ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የሀገርን ከፍታ ለማረጋገጥ መፍጠን፣ መፍጠር፣ ማብዛት እና ያንንም በጥራት አሳድጎ መስራት እንደሚገባም ተመላክቷል
የኢትዮጵያን የታሪክ ምዕራፎች በትዝታ አክናፍ በእውነት መዳፍ ከፊት ወደ ኋላ ገለጥ ገለጥ ብናደርግ ከአክሱም ሀውልት እስከ ላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ከሶፍ ኡመር ዋሻ እስከ ጀጎል ግንብ፣ ከጥያ ትክል ድንጋይ እስከ ሀላላ ኬላ …፣ ከዘርያዕቆብ የፍልስፍና ምጥቀት እስከ አባ ጅፋር የቴክኖሎጂ ዕውቀት… ከፍ ከፍ ያሉ አያሌ የሀገር አብነቶችን መጥቀስ እንችላለን።
ይሁን እንጂ የአክሱም ሀውልትን ከወጥ ድንጋይ ያነፀው፣ ቤትን ከጣሪያ ጀምሮ በመሰራት መጨረስ እንደሚቻል ላል ይበላን ሰርቶ የዓለምን የህንፃ አሰራር ጥበብ ፉርሽ ያደረገው ያ! ትውልድ መፍጠኑን አቁሞ፣ መፍጠሩን ትቶ፣ ማብዛቱን እና ማጥራቱንም ዘንግቶ እንዴት ባለበት ቆመ! ስልጣኔን ቀድሞ ጀምሮ ለምን ጭራ ሆነ! የሚለውን ስናስብ ነገሩ ውስብስብነት ባያጣውም እጅጉን የሚያስቆጭ መሆኑ ግን አያጠያይቅም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንኑ እውነት ከነ መፍትሔው ጭምር በመደመር መፅሐፋቸው መግቢያ አስፍረውታል፡፡
ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ!” በሚል መሪ ቃል ለከፍተኛ አመራሮች ስልጠና መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለመፍጠር ሲያብራሩ፣ ብዙ ያልፈጠረ ጥራትን ማረጋገጥ አይችልም ብለዋል፡፡ እናም ከብዙ ፈጠራ ውስጥ ጥራት ያላቸው ጉዳዮች እንደሚወጡ አንስተዋል።
ብዙ ለመፍጠርም ፍጥነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፣ ያልፈጠነ ጊዜው እንደማይጠብቀው አጽንኦት ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዛት፣ እድል እና ጥራት ግን ውጤት መሆኑን በማንሳት በብዙ ፈጠራ ውስጥ አዳዲስ እና ጥራት ያላቸው ነገሮችን ከብዙው ውስጥ መዝዞ ማውጣት እንደሚቻልም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አክለውም፣ በብዙ ፈጠራ ውስጥ ዘላቂ ውጤትን ማስቀጠል እንደሚቻል የገለጹ ሲሆን፣ በብዙ መፍጠር ውስጥ በመፍጠን ጥራትን ማረጋገጥ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን ለማሻገር በመደመር መንግስት እሳቤዎች በመታገዝ፣ በመፍጠን መርህ፣ በመፍጠር እሳቤ፣ ፈጠራንም በማብዛት እና ያንንም በጥራት አልቆ በመስራት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያና አማካሪ አቶ በረከተአብ ተስፋዬ እንደሚሉት እንደ ሀገር ኢኮኖሚያዊ አቅማችንንም ሆነ ሌሎች ዘርፎችን የበለጠ ለማላቅ ከኢትዮጵያ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ታሪካዊ ዕውነታዎች እና ያለፈው ትውልድ የከወናቸው የዕድገትና የአብሮነት እርሾዎችን ከግምት በማስገባት ከዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አቅጣጫን መከተል ይገባል፡፡
በመሆኑም መንግስት ያስቀመጣቸው “መፍጠር፣ መፍጠን፣ ማብዛት እና ማጥራት” የሚሉ አራት የማይነጣጠሉና የሚደጋገፉ እሳቤዎች ሀገርን ከታሪካዊ መቀዛቀዝ አውጥቶ ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር የሚያግዙ የዕድገት ቀመሮች ናቸው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አራቱን ምሶሶዎች አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያም መፍጠር፣ አዳዲስ ሐሳቦችንና መፍትሔዎችን በማመንጨት የሥራ እና የልማት መስኮችን ማስፋት ነው። የልማት ሥራዎችንና የለውጥ እርምጃዎችን በከፍተኛ ፍጥነትና ቅልጥፍና መፈጸምም ነው።
ማብዛት ደግሞ የተገኙ መልካም ልምዶችንና ስኬቶችን በስፋትና በተደራጀ መልኩ ማስፋፋት ሲሆን፣ ይህም የሥራ አፈጻጸምን፣ ስርዓቶችን እና ውጤቶችን ያለማቋረጥ በማሻሻል ጥራትን ማረጋገጥ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያው በረከተአብ ምልከታ ይህ ፍልስፍና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጠንካራ አመራር እና ኢትዮጵያን የመለወጥ ራዕይ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፣ የሀገሪቱን ታሪካዊ ኃይልና የህዝቧን ተስፋ ወደ ተግባራዊ ውጤት ለመቀየር የሚያስችል የዕድገት ሞዴል መሆኑን ከለውጡ ወዲህ በግብርናው፣ በኢንደስትሪው፣ በቱሪዝም እና መሰል ዘርፎች እየታዩ ያሉ ውጤቶችን በአስረጂነት መጥቀስ እንደሚቻልም ገልፀዋል፡፡
የኢኮኖሚ ዕድገት የሚጀምረው እሴት በመፍጠር ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ በረከተአብ፣ አዳዲስ ድርጅቶች፣ አዳዲስ የምርት መስመሮች፣ አዳዲስ አገልግሎቶች እና ቴክኖሎጂዎች በፍጥነት፣ በጥራት፣ በማብዛት እና በመፍጠር መስራት ሲቻል ነው፡፡
ለአብነትም ፈጠራ የኢኮኖሚውን ምርታማ ድንበር ይጨምራል፤ የሥራ ዕድልን ያሰፋል፤ የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ በመጨመር ምቹ ኑሮን እንዲያጣጥሙ ያደርጋል፤ ከዚህ ባሻገርም ከራስ ተርፎ ምርቶቻችንን በስፋት ለዓለም ገበያ አቅርበን የበለጠ ተጠቃሚ እንድንሆን ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ፍጥነት ለሀገር የኢኮኖሚ ከፍታ አስፈላጊ ነው ስንል መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ እንቅፋቶችን በመቅረፍ ምርትና ምርታማነትን ከፍ በማድረግ ፈጠራ ብቻውን እንዳይቆም ይልቅም እንዲበዛ ያደርጋል ሲሉም አክለዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንደሚሉት መፍጠር፣ መፍጠን፣ ማብዛትና ማጥራትን በመጠቀም ሲንጋፖርን የመሳሰሉ ሀገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕድገታቸውን ማላቅና በዓለም ኢኮኖሚ ሚዛንም ከፍ ብለው መገኘት ችለዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ ተአምራዊ ዕድገትም በድንገት የተመዘገበ ሳይሆን እንደ ሀገር ያላቸውን ሁለንተናዊ አቅም በመፈተሽ፣ በተለይም የኢንደስትሪዎቿን ችግር በመቅረፍ አቅማቸውን በማላቅ እና የተትረፈረፈ ምርት እንዲያመርቱ በማበረታታት ነው፡፡ በመሆኑም ደቡብ ኮሪያ ያደገችው ብሔራዊ የኢንዱስትሪ አቅምን በማፋጠን፣ ፈጠራን በማብዛት፣ ምርትና ምርታማነትን በስፋት እና ጥራትን መሰረት አድርጎ በመስራት እንደሆነም የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
አፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳም፣ ከችግር በኋላ መፍጠን፣ መፍጠር፣ ማብዛትና ማጥራት በመቻሏ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከችግሮቿ ተላቅቃ የለውጥ ተምሳሌት መሆን እንደቻለችም ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ በፈጠራ የታገዙ አዳዲስ የእድገት ሞተሮች ያስፈልጓታል፡፡ ምክንያቱም ካለው አቅም አንፃር ሲመዘን ዝቅተኛ ምርታማነት ያለው ግብርና፣ ውስን ማኑፋክቸሪንግ፣ ከውጭ በሚገቡ እቃዎች ላይ ጥገኛ መሆን፣ ከፍተኛ የወጣቶች ስራ አጥነት ስላለባት ይህንን ችግር በሚገባ ለመቅረፍ ግድ መፍጠር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በመሆኑም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች (ማኑፋክቸሪንግ፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ የግብርና ማቀነባበሪያ)፣ አዳዲስ የኤክስፖርት ምርቶች፣ በገጠር እና በከተማ አካባቢዎች አዳዲስ ስራዎች፣ አዳዲስ የፈጠራ ማዕከላት እና የምርምር እና ልማት ማዕከላት፣ አዳዲስ ዘርፎችን መፍጠር፣ ማብዛት፣ ማጥራት እና መፍጠን እንዳለባትም ጠቁመዋል፡፡
ፍጥነት ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍታ ያስፈልጋል ስንል ብዙ ተጨባች ምክንያቶች ስላሉን ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ ለአብነትም ዓለም በከፍተኛ ፍጥነት በሚመራ የዕድገት መስመር ላይ በመሆኑ ተወዳዳሪ ለመሆን የግድ መፍጠን ይኖርብናል፡፡ በሌላ በኩል ከለውጡ ወዲህ የመጡና እየታዩ ያሉ ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆኖ የዘገየ የፕሮጀክት ትግበራ፣ የቢሮክራሲያዊ እንቅፋቶች፣ የፋይናንስ ተደራሽነት ችግር፣ የኃይል እጥረት እና መሰል ችግሮች ይስተዋላሉ፤ በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ ፍጥነት የግድ ይለናል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ፍጥነት የልማት ፕሮጀክቶችን ወጪ ይቀንሳል፣ መንግስት በፍጥነት እርምጃ ሲወስድ ባለሀብቶች በራስ መተማመን ያገኛሉ፤ ፈጣን የመሠረተ ልማት ዕድገት ምርታማነትን ይጨምራል፤ ሰፋፊ የስራ ዕድልን መፍጠር እንደሚያስችልም ተናግረዋል፡፡
እንደ ሩዋንዳ፣ ቬትናም እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ በፍጥነት የተንቀሳቀሱ ሀገራት ድህነትን በአጭር ጊዜ እያሸነፉ መምጣታቸውን የጠቀሱት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ በረከተአብ፣ ኢትዮጵያም የኢኮኖሚ ከፍታዋን በሚገባ ታረጋግጥ ዘንድ መፍጠን፣ መፍጠር፣ ፈጠራንም ማብዛት እና ያንንም በጥራት አልቆ መስራት ይኖርባታል ብለዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ