ኢትዮጵያና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ80 ዓመታት ግንኙነት እና ትብብራቸዉን በጋራ አከበሩ

You are currently viewing ኢትዮጵያና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ80 ዓመታት ግንኙነት እና ትብብራቸዉን በጋራ አከበሩ

AMN ህዳር 27/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምሥረታና እንደ መሥራች አባል የነበራትን ሚና 80ኛ ዓመት በኩሪፍቱ አፍሪካ ቪሌጅ በደማቅ የባህል ምሽት አስታውሳለች።

ይህ ዝግጅት የ“ኢትዮጵያ ወር” ክብረ በዓላት አካል ሲሆን፣ አምባሳደሮችን፣ ሚኒስትሮችን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችንና ባለድርሻዎችን አሰባስቧል።

ምሽቱ የኢትዮጵያን ባህላዊ ዕሴት እና ሀብት በማጉላት የ80 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ትብብርንና የጋራ ቃል ኪዳኖችን አክብሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የባህል ዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ያለውን ጠቀሜታ አጽንኦት ሰጥተው፣ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅ ምሥረታ ውስጥ የነበራትን ታሪካዊ ሚናና ለባለብዙ ወገን ሥርዓት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

አፍሪካ በአየር ንብረት፣ ሰላም ጥበቃና ልማት ላይ ያላትን እያደገ የመጣ ሚና በማጉላት የተመድ ሁሉንም አካታች በሚያደርግ መንገድ ማሻሻያዎችን ማድረግ እና አሁን ላይ እያጋጠሙ ላሉ ፈተናዎች መፍትሔ መስጠት በሚችልበት ቁመና ራሱን ማጠናከር እንደሚገባው ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተቀማጭ ሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ አቡባከር ካምፖ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከተመድ ጋር ያላት አጋርነት ገና ከምሥረታው ጀምሮ በሠላም ማስከበር ተሳትፎ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነትን በማላቅ የአፍሪካን አንድነት በማጠናከር የተገለጸ እንደሆነ አብራርተዋል።

በመጪው የትብብር ማዕቀፍ (2025-2030) በኩል ሰላምን ለማስፈን፣ ተጋላጭ ማህበረሰቦችን ለመጠበቅ፣ ሴቶችና ወጣቶችን ለማብቃት፣ ተቋማትን ለማጠናከር ተመድ የረጅም ጊዜ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ምሽቱ ባህላዊ ሙዚቃ፣ ዳንስ፣ ትርኢትና የኢትዮጵያ ምግቦችን በማቅረብ ባህልን ከዲፕሎማሲ ጋር የሚያዋህድ ድባብ የፈጠረ እንደነበር ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review