AMN – ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የኢኮኖሚ እና የንግድ ግንኙነታቸውን ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ ተገለጸ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ረዳት ሚኒስትር ከሆኑት ማርክ ሚቸል ጋር ተወያይተዋል፡፡
መሪዎቹ በኢትዮጵያ ቀጣይነት ባላቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ በኢንቨስትመንት ዕድሎች እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተመካክረዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ እና የመዋቅራዊ ማሻሻያ አጀንዳ አጠቃላይ ሁኔታዎችን ያስረዱ ሲሆን፤ ለግሉ ሴክተር ልማት እና ለቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡትን ጠቃሚ እመርታዎች አንስተዋል።
አክለውም የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ፣ የንግድ ሥራ ከባቢን ለማሻሻል እና ለአለም አቀፍ ባለሀብቶች የሚሰጡ ዕድሎችን ለማስፋት የተጀመሩ ማሻሻያዎችን ለማስቀጠል መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ማርክ ሚቸል በበኩላቸው በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ስር የተመዘገበውን እድገት ያመሰገኑ ሲሆን፤ የኢንቨስትመንት ከባቢን ለማሻሻል መንግሥት እያደረገ ባለው ጥረት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ የገለጹት ሚስተር ሚቸል፤ በአሜሪካ ኩባንያዎችና በኢትዮጵያ ገበያ መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር የአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች የሁለትዮሽ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነቶችን ለማስፋት፣ የግሉ ሴክተር አጋርነቶችን ለማጠናከር እና የንግድ ለንግድ ግንኙነቶችን ከፍ ለማድረግ በሚያስችሉ ዕድሎች ላይ ሐሳብ ተለዋውጠዋል።
በተጨማሪም በአዲሱ የአውሮፕላን ማረፊያ ልማት ፕሮጀክት እና የአሜሪካ የፋይናንስ ተቋማት ይህንን ታላቅ እቅድ ለመደገፍ ባላቸው ፍላጎት ላይ ተወያይተዋል።
ሁለቱም ወገኖች አዳዲስ የኢኮኖሚ ትብብር መስኮችን እና የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ በቀጣይነት መወያየትና መተባበር አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
በመጨረሻም ሁለቱም ወገኖች በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ እና የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር፣ እንዲሁም በቀጣዮቹ ዓመታት የኢንቨስትመንት እና የንግድ ትብብርን ለማበረታታት የሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ማረጋገጣቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።