የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሪፎርም እና የኢ-ካርታ ስኬት

You are currently viewing የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሪፎርም እና የኢ-ካርታ ስኬት

‎AMN ሕዳር 29/2018 ዓ.ም

‎በ2016 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሪፎርም ከተደረገባቸው ተቋማት ውስጥ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አንዱ ነው።

‎ቢሮው ቀደም ሲል ይጠቀምበት የነበረውን የኦንላይን ቴነር ማኔጅመንት ሲስተም በማሻሻል ወደ ተቀናጀ የመሬት መረጃ አስተዳደር ሥርዓት (Integrated Land Information Management System – ILIMS) አድጓል።

የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ መኮንን ያኢ በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ እንደገለጹት፣ ከ2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከ35 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ባለይዞታዎች የኢ-ካርታ አገልግሎት መስጠት ተችሏል።

በ2018 ዓ.ም. ተሻሽሎ ወደ ሥራ የገባው የተቀናጀ የመሬት መረጃ አስተዳደር ሥርዓት ፈጣን እና ቀልጣፋ የኦንላይን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው።‎ ከዚህ በፊት ያልነበሩ አዳዲስ አገልግሎቶች ማስጀመራቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ከእነዚህም መካከል የኮንዶሚኒየም፣ የአፓርትመንት እና የሪል እስቴቶች የወልና የተናጠል ካርታ ኅትመት ይገኝበታል።

ይህም የቆየውን የኮንዶሚኒየም ኢ-ካርታ አገልግሎት ተግዳሮት በአዲስ መልክ ለመፍታት የሚያስችል ሲሆን፤ እስካሁን ድረስም ከ680 በላይ ካርታዎች ታትመዋል። ‎በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ 13 ሞጁሎች ተሻሽለውና አዳዲስም ተሠርተው ወደ ሥራ ገብተዋል ።

በዚህም ከ3,100 በላይ የኢ-ካርታ፣ የዕግድና የስም ዝውውር አገልግሎቶች መስጠት ተችሏል።ሲስተሙን ይበልጥ ለማጠናከር ሲባል የዲጂታል አርካይቭ ማኔጅመንት ሲስተም እና የሞባይል አፕ አገልግሎቶች ተካተው እንዲለሙ ተደርጓል፤ ይህም የሲስተሙን አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጓል።

‎‎አዲሱና ተሻሽሎ የለማው የተቀናጀ የመሬት መረጃ አስተዳደር ሲስተም ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ጋር በሚመጣጠን መልኩ ተዘጋጅቷል።

‎ይህም ማለት ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ክፍተቶችን በቀላሉ ማሻሻል በሚያስችል አግባብ ነው የተዋቀረው።

‎ኃላፊው ይህ ሲስተም ጠንካራ ተቋማዊ ቅንጅት እንዲፈጠር የሚያግዝ እና የኦንላይን አገልግሎቶችን የሚያሳልጥ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህ የተቀናጀ የመሬት መረጃ አስተዳደር ሲስተም በሙሉ አቅሙ ወደ ተግባር ሲገባ፣ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የቴክኖሎጂ ትስስር ይፈጥራል።

እነዚህ ተቋማትም ከፕላንና ልማት ቢሮ፣ ከግንባታ ፈቃድና ባለሥልጣን፣ ከመንግስትና የግል ባንኮች፣ ከፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫ እና ከሲቪል ምዝገባና የነዎሪነት አገልግሎት ተቋማት ጋር ቅንጅት ይፈጥራል።

‎ይህም የኦንላይን አገልግሎቶችን በማሳለጥ ለዜጎች የሚሰጠውን የመሬት አስተዳደር አገልግሎት ጥራት ያሻሽላል ተብሏል ።

‎በ ዘዉድነህ አብዲ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review