ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የባለብዙ ወገን ግንኙነት ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሁ ቻንቹን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚነስትሩ ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ገፀ ብዙ የመሆኑን አስፈላጊነት በመግለጽ:ለልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን፣አካባቢያዊ ሁኔታዎችን እና አጠቃላይ ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር እንዲፈጠር እያደረገችው ያለውን ጥረት በተመለከተ ገልጸውላቸዋል።
አምባሳደር ሁ ቻንቹን በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የደረሰ እና ዲፕሎሜሲያዊ ግንኙነታቸውን የመሠረቱበት 55ኛ ዓመት መድፈኑን አስታውሰዋል።
አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የባለብዙ ወገን ግንኙነት ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል። ሁለቱ ወገኖች የጋራ ፍላጎት ባላቸው መስኮች ዙሪያ በቅርበት መሥራታቸውን አጠናክሮ ለመቀጠል መስማማታቸዉን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡