ማስተር አብነት ከበደ ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን እንደሚቻል ካስተማሩ ሰዎች መካከል አንዱ ነው። በሚሠራው የበጎ አድራጎት ሥራ የተቸገሩ ሰዎችን ሕይወት መለወጥ እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ሰው ነው።
ከሚያለቅሱ እናቶች ጋር ሲያለቅስ፣ ከታማሚዎች ጋር አብሮ ሲታመም፣ በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ የሚታወቀው ማስተር አብነት ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቅሞ እርዳታዎችን በማሰባሰብና በመለገስ የብዙዎችን እንባ አብሷል።
አሁን ግን ማስተር አብነት ራሱ በከባድ ሕመም ላይ መውደቁን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበረው ቆይታ ይፋ አድርጓል።
“ችግረኞችን ለመርዳት ገንዘብ እያሰባሰብኩ ዝም ብዬ መቀመጥ አልችልም” የሚለው ማስተር አብነት የሕመሙን ምንነት ለይቶ ባያስቀምጥም ስለመታመሙ ለማንም መናገር እንደማይፈልግ ገልጿል።

ማስተር አብነት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ 30 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ 5 ሰዎችን ለሕክምና ወደ ሕንድ ሀገር ሔደው እንዲመለሱ ማድረግ ችሏል።
“እኔ አሁን ባልተመረመረ በሽታ ውስጥ ነው ያለሁት፣ የሚያስጨንቀኝ ይሄ ሕመም በምርመራ አይገኝም፣ ራሴን እያጣሁ፣ በሥነ-ልቦናም እየተጎዳሁ ነው” ብሏል።
ማስተር አብነት ማንንም ሰው ማስጨነቅ ስለማይፈልግ ብቻ ስለሕመሙ ጉዳይ ባይገልጽም የለበሰው ልብስ የሸፈነውና በህክምና ይህ ነው የማይባል ሕመም እያስጨነቀው ይገኛል። አሁን ላይ ግን መታመሙ ከእሱ አልፎ በሌሎች ዘንድ እየታወቀ በመምጣቱን ብዙዎች እየጠየቁት እንደሆነ ተናግሯል።

“የእናቶችና የአባቶች እንባ ሲታበስ ማየት፣ ወንድሜ አንገቱን ቀና አድርጎ ሲሄድ ማየት፣ የኩላሊት ሕመም የነበረባት እህቴ ተሽሏት ፈገግታዋ ሲመለስ ከማየት በላይ የሚያስደስተኝ ነገር የለም። ያንን አይቼ እጽናናለሁ” ብሏል።
ማስተር አብነት “የውስጤን በሽታ ፈጣሪ እንደሚያድነኝ አምናለሁ” በማለት ከዚህ ውጪ ሰው ማስጨነቅ ስለማልፈልግ የኢትዮጵያ ሕዝብ፥ አባቶች እና እናቶች እንዲጸልዩለት ጠይቋል።

ከጊዜ በኋላ የሕይወቱን ትርጉም በበጎ አድራጎት ሥራ ውስጥ ያገኘው ማስተር አብነት ዛሬ ላይ ለተቸገሩ ድምጽ እና የተስፋ ድልድይ በመሆን በፌስቡክ ላይ ከ1.7 ሚሊዮን፥ በቲክቶክ ደግሞ ከ4.8 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ማፍራት የቻለ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ችሏል።
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክም ለማስተር አብነት ሙሉ ጤንነቱ እንዲመለስለትና ወደሚወደውና ለብዙዎች ሕይወት ተስፋ ወደሆነበት የበጎ አድራጎት ሥራው እንዲመለስ ይመኛል።