የዲፕሎማሲው ከፍታ

You are currently viewing የዲፕሎማሲው ከፍታ

የኢትዮጵያ እና የህንድ ግንኙነት ከሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ እስትራቴጂካዊ አጋርነት እየተሸጋገረ መሆኑ ተመላክቷል

ኢትዮጵያ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ደማቅ ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ በመሆኑም ከዓለም ሀገራት ጋር ያላት የውጭ ግንኙነት ዘለግ ያለ ዕድሜን አስቆጥሯል። በተለይ ሀገሪቱ ካለችበት ስትራቴጂካዊ መልክዓ ምድር አቀማመጥ አኳያ ለዲፕሎማሲ ግንኙነት የበለጠ ተመራጭ ሀገር ሆናለች፡፡

በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት፣ የዕድገት፣ የሰላምና የዲፕሎማሲ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን የዓለማችን ታላላቅ ሀገራትና ተቋማት አብዝተው ይፈልጓታል፡፡ በተለይም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተከፈቱ ምቹ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ በሮች አዲስ አበባ፣ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት ያላቸውን የውጭ ሀገር መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችን እና የተለያዩ ጎብኝዎችን በየቀኑ በሚባል ደረጃ እያስተናገደች ነው።

ኢትዮጵያ ከዓለም ታላላቅ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነትና ተሳትፎም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ከሰሞኑም የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ከፍታ እየጨመረ መምጣቱን ያመላክታል ይላሉ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት እና በህንድ ሀገር የተማሩት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ዘላለም ግርማ (ዶ/ር)።

ባሳለፍነው ማክሰኞም (ታህሳስ 8 ቀን 2018 ዓ.ም) ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢፌዴሪ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ እና ህንድ ግንኙነት 2 ሺህ ዓመታትን ማስቆጠሩን ጠቁመው፣ ደማቅ ታሪክና ባህል የሚጋሩ ሀገራት መሆናቸውን አውስተዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ህንድ ለኢትዮጵያ የልማት ጉዞ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ያረጋገጡ ሲሆን፣ በተለይም በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሳይበር ሴኩሪቲ፣ በአቅም ግንባታ፣ በግብርና፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች በትብብር ለመሥራት ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላትም አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣናዊ ሰላምና ጸጥታ ዘርፍም የህንድ እና የኢትዮጵያ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም መሠረት በይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል። ከዓድዋ ድል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያውያን ቅኝ ላለመገዛት በልበ ሙሉነትና በአንድነት ያደረጉት ተጋድሎና ያገኙትን ድልም አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ አሁንም በቀጣናው ያላት የሰላምና መረጋጋት ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ያደነቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ፣ በዓለም መድረኮችም ህንድና ኢትዮጵያ ያላቸውን ድምፅ በማስተባበር ለአዳጊ ሀገራት መብት መከበር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡

የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ዘላለም ግርማ (ዶ/ር)፣ ህንድ አህጉር በሚባል ደረጃ ትልቅ ሀገር እንደሆነች ጠቅሰው፣ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ህዝብ ይኖርባታል። ይህንንም ተከትሎ ህንዳውያን ብዙ ባህልና ማንነት አላቸው፡፡ በዚህ ልክ ከገዘፈ ሀገር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማጠናከር ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት ብለዋል፡፡

ህንድ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ኢኮኖሚያቸውን በፍጥነት ከፍ እያደረጉ ካሉ ጥቂት ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በተለይም ሀገሪቱ በአገልግሎት ዘርፍ እድገት እና ጉልህ በሆኑ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ምክንያት እየተለወጠች መሆኑን የገለፁት ባለሙያው፣ ከግብርና ወደ አገልግሎት መር ሞዴል በመሸጋገር ለዓለም አቀፍ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡ ምቹ የሆነ የማኑፋክቸሪንግ እና የአቅርቦት ሰንሰለት ማዕከል እየሆነች መምጣቷንም ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ የምትከተለው የፌዴራሊዝም ስርዓት ነው፡፡ ህዝቦቿ ተቻችለው፣ ተረዳድተው እና ለአንድ ሀገራቸው ከፍታ በጋራ የሚቆሙበትና የሚሰሩበት ድንቅ ባህል አላቸው  የሚሉት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ዘላለም (ዶ/ር)፣ በሀገሪቱ በነበራቸው ቆይታ እንደታዘቡት የአንዱን ባህል አንዱ ያከብራል፣ ድሃውም ሀብታሙም እኩል እየተረዳዳ የሚኖርባት፣ የሀገሪቱ መንግስት ሀብቱን ለድሃው የሚያውልበት እና መንግስትና ህዝብ ግልፅ የሆነ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ ህዝቡ ችግር ቢያጋጥመው እንኳን በውይይት ለመፍታት የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ህንዳውያን ጠንካራ የስራ ባህል እንዳላቸው የጠቀሱት ዘላለም ግርማ (ዶ/ር) ከህንዳውያን እነዚህን መልካም ነገር ልንማር እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

የፖለቲካ ስርዓታቸውም ሆነ ግንዛቤያቸው ህንዳውያንን የሚያስተሳስር መሆኑን የጠቆሙት ዘላለም (ዶ/ር) ለአብነትም፣ ገዥው ፓርቲ ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍሎች በጋራ የሚያስተዳድሩበትም ሁኔታ አለ፡፡ ይህም የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል ከህንዳውያን ልንማረው የሚገባ መሆኑን እና ኢትዮጵያም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በዚህ ምዕራፍ ላይ መሆኗን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢፌዴሪ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ “ዛሬ በእናንተ ፊት ቆሜ ንግግር ማድረግ በመቻሌ ከፍተኛ ክብር ይሰማኛል” ብለው፣ ምድረ ቀደምትና የሰው ዘር መገኛ በሆነች ኢትዮጵያ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ፤ በመሆኑም ወደ ቤታቸው እንደመጡ ያህል ደስታ እንደተሰማቸውም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ አቻቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅ ‘የኢትዮጵያ ክብር ኒሻን’ በመቀበላቸውም በህንድ ሕዝብ ስም የተሰማቸውን ደስታ የገለፁ ሲሆን፣ ሽልማቱን በታላቅ ትህትና በህንድ ሕዝብ ስም መቀበላቸውን በታላቅ ምስጋና ገልፀዋል፡፡

በእርግጥም ህንድ እና ኢትዮጵያ ወዳጅነታቸው በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ታሪክ ብንነሳ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት አንስቶ የህንድ መምህራን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ማስተማር ጀመሩ፡፡ ህንዳዊያኑ ለንጉሱም ከትምህርት ስርዓት ጋር በተያያዘ የማማከር አገልግሎት ሲሰጡ ስለመቆየታቸው መረጃዎች ያመላክታሉ። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት በህንድ ኤምባሲዋን የከፈተች የመጀመርያ ሀገርም ናት፡፡

ህንድ መምህራንን ወደ ኢትዮጵያ መላክ ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም ወደ ህንድ ሄደው እንዲማሩ ነጻ የትምህርት እድል ትሰጣለች። ይህንን ታሪካዊ ትስስርም  ባሳለፍነው ማክሰኞ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢፌዴሪ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር አውስተዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ከዚህም የተሻገረ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ ለአብነትም በህንድ ታሪክ ውስጥ እጅግ ታዋቂ የሆነው ኢትዮጵያዊ ንጉስ ህንድን ከ1548 እስከ 1626 እ.ኤ.አ  ያስተዳደረው ማሊክ አምባር ከጥንታዊው የሀገራቱ ትስስር በቀዳሚነት ይጠቀሳል። የማሊክ አምባር ሙዚየም እስካሁንም በምዕራብ ህንድ ‘የቅዱሳን ሸለቆ’ በመባል በምትታወቀው ጥንታዊቷ ኩልዳባድ ከተማ ይገኛል፡፡

በዚህ ሙዚየም ውስጥ ኢትዮጵያዊው የህንድ ንጉስ ማሊክ አምባር ይጠቀምባቸው የነበሩና ኢትዮጵያን የሚገልፁ ልብሶችም ይገኛሉ ይላሉ የአፍሪካ ዲያስፖራዎችን ታሪክ በመጻፍ የሚታወቁት ፕሮፌሰር ኦማር ኤች. አሊ “Malik Ambar:  Power and Slavery across the Indian Ocean” በተሰኘው መፅሐፋቸው፡፡

በህንድና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ከፍ እያለ የመጣ ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከውጭ ለሚገቡ ኢንቨስትመንቶች የምታደርጋቸው ማበረታቻዎች በምክንያትነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን የፖቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ መሐመድ በሽር ይናገራሉ፡፡

ታህሳስ 8 ቀን 2018 ዓ.ም የኢትዮጵያና ህንድ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ፎረም እንደተገለፀው፣ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ መጠን በአማካይ 1 ነጥብ 79 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ኢትዮጵያ በዋናነት አኩሪ አተር፣ ቦሎቄና ሌሎች የቅባት እህሎችን ወደ ህንድ የምትልክ ሲሆን ሩዝ፣ ስኳር፣ ክትባትና ሌሎች የሕክምና ግብዓቶችን ከህንድ ከምታስገባቸው ምርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

በዚሁ መድረክ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ከ600 በላይ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ የህንድ ኩባንያዎች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን፣ ህንድ በኢትዮጵያ ውስጥ  ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ካስመዘገቡ ሀገራት ውስጥ ሁለተኛውን ደረጃ እንደያዘችም ተመላክቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው ህንድ ኤምባሲ  ጥቅምት 31 ቀን 2025 እ.ኤ.አ “የህንድ እና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች” (INDIA- ETHIOPIA BILATERAL RELATIONS) በሚል ርዕስ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ በአክሱማይት ስርወ መንግስት ወይም ከ1ኛው መቶ ክፍለ ዘመን  ጀምሮ የበለጠ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡

እ.ኤ.አ በ1950 ሳርዳር ሳንት ሲንግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የህንድ አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ በሀገራቱ መካከል በዘመናዊ መልኩ ሙሉ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተጀምሯል ይላል መረጃው፡፡

ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ታሪካዊ ትስስርን ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች ትልልቅ ፋይዳ ያላቸውን ስምምነቶችን እንዳደረጉ የህንድ ኤምባሲ ይፋ ባደረገው መረጃ ተመላክቷል፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ እ.ኤ.አ ከ2023 እስከ 2024 ባለው ጊዜ ህንድ ወደ ኢትዮጵያ የላከችው ምርት 489 ነጥብ 59 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ያስገባችው ምርቶች ደግሞ 81 ነጥብ 93 የአሜሪካ ዶላር እንደነበር የሚያትተው የኤምባሲው መረጃ፣ ህንድ በዓለማችን ለኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ትልቁ የንግድ አጋር እንደሆነችም አመላክቷል፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽን፣ ጤና እና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከሁለቱ ሀገራት አበይት የትብብር መስኮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሲያደርጉ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከማንሞሃን ሲንግ በኋላ ኢትዮጵያን የጎበኙ ሁለተኛው የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ህንድ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ጋር ያላትን የልማት አጋርነት ማሳደግ ትልቅ አቅም እንዳለው እና የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ከፍታ የሚያሳይ መሆኑን ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ሙሐመድ በሽር ይናገራሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ይፋዊ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ማድረጋቸውን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል በጉምሩክ የጋራ አስተዳደር ድጋፍ፣ በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳታ ማዕከል ምስረታ የመግባቢያ ሥምምነቶችን እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ላይ ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እና የሚያጠናክረውን የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ሥራ የመግባቢያ ሥምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይም ተገኝተናል ብለዋል።

“ህንድ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ አጋር ስትሆን፣ የዛሬዎቹ ውይይቶች እና ሥምምነቶችም ለጋራ ጥቅም በተለያዩ ዘርፎች ያሉንን ትብብሮች ለማስፋት ያለንን የጋራ ቁርጠኛ አቋም ያሳያሉም ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በእርግጥም ኢትዮጵያና ህንድ ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ፣ ዘመን ተሻጋሪ እና ከፍታውን የጠበቀ መሆኑን በአዲስ አበባ ከሚገኘው ጋንዲ ሆስፒታል እስከ ኢትዮጵያዊው የህንድ ንጉስ ማሊክ አምባር ሙዚየም ድረስ አያሌ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review