በአዲስ አበባ የተከናወኑ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የጎርፍ ስጋትን በዘላቂነት እየቀነሱ ነው

You are currently viewing በአዲስ አበባ የተከናወኑ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የጎርፍ ስጋትን በዘላቂነት እየቀነሱ ነው

AMN – ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በከተማዋ በወንዞች እና የወንዝ ተጎራባች አካባቢዎች የተከናወኑት ልማቶች የጎርፍ ስጋትን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውን ገልጿል።

የኮሚሽኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በስራው መሰለ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ፣ የወንዞች ዳርቻዎች ልማቶች ለአደጋ ስጋት ስራ አመራር ያላቸው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ ቀደም በደለል የሚሞሉ፣ ውሃ አቁረው ከፍተኛ አደጋዎችን ያስከትሉ የነበሩ እንደ ቀበና ወንዝ ያሉ አካባቢዎች አሁን ላይ ከአደጋ ስጋት ነፃ እየሆኑ መምጣታቸው ገልጸዋል።

በወንዝ ዳርቻዎች ላይ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች እና የሚተከሉ ችግኞች የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት በመቀነስ ረገድ ምቹ መደላደል መፍጠሩን አቶ በስራው ጠቅሰዋል።

የመሬት እና የአፈር መሸርሸር እንዲሁም የመሬት መደረመስ አደጋዎችን በመከላከል በኩልም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

አብዛኛዎቹ የለሙ አካባቢዎች ለአደጋ ጊዜ አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እንደ አምቡላንስ እና የእሳት አደጋ መኪኖች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ዘርዝረዋል።

ቀደም ሲል ለድንገተኛ አደጋዎችና ለጸጥታ ስጋት የተጋለጡ የነበሩ አካባቢዎች አሁን ላይ መብራት ተዘርግቶባቸው፣ በቀንም ሆነ በማታ በህዝብ እንቅስቃሴ ተሞልተው ማህበረሰቡ የሚዝናናባቸው እና ደህንነቱ የተረጋገጠባቸው ስፍራዎች ሆነዋል።

የወንዝ ዳርቻ ልማቱ በቁጥር ሊገለጽ ከሚችለው በላይ በማህበራዊ፣ በአደጋ ስጋት ስራ አመራር፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና በኢኮኖሚ ዘርፍ ትልቅ ፋይዳ ያለው እንዲሁም ለትውልድ የሚሻገር ስራ መሆኑን የኮሚሽኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በስራው መሰለ ተናግረዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review