በፈረንጆቹ 2025 ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ የሰሀራ በታች የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፏን የደቡብ አፍሪካው “ቻናል አፍሪካ” ዘግቧል።
በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር በፈረንጆቹ 2025 የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በማፋጠንና የኢንቨስተሮችን ዕምነት በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡንም ገልጿል።
የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ስርጭት ኮርፖሬሽን (SABC) አካል የሆነውና በመላው አፍሪካ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚታወቀው “ቻናል አፍሪካ” እንደገለጸው ኢትዮጵያ ከዓመታት ግጭት፣ የብድር ጫና እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በኋላ አሁን ላይ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እያሳየች ትገኛለች።
ዘገባው የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ጋር የጀመረው የታደሰ ግንኙነትና ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረጉ የኢንቨስተሮችን ዕምነት ለመመለስ አስችሏል።

በተለይም ቀደም ሲል በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበሩት የቴሌኮሙኒኬሽንና የፋይናንስ ዘርፎች ወደ ግል ይዞታነት እንዲሸጋገሩ የተደረገው የሊበራላይዜሽን ሒደት ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተናግሯል።
ሀገሪቱ ያሳለፈቻቸው ወሳኝ የሽግግር ስኬቶች ዓለም አቀፍ መተማመንን በመመለስ ለዘላቂ ዕድገት ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም ገልጿል።
“ቻናል አፍሪካ” በዘገባው እንደጠቀሰው ምንም እንኳን የዋጋ ንረት፣ ሰላምን የማጽናት አስፈላጊነትና የኢኮኖሚ ዕድገቱ ተጠቃሚነት ሁሉም ሕዝብ ጋር የማድረስ ተግዳሮቶች ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት የተከናወኑት ማሻሻያዎች ኢትዮጵያን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተሻለና በጽኑ የዕድገት ጎዳና ላይ አቁመዋታል።
“ቻናል አፍሪካ” የአፍሪካን አወንታዊ ገጽታና ወቅታዊ ለውጦች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማድረስ የሚታወቅና በደቡብ አፍሪካ መንግሥት ስር የሚተዳደር ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚዲያ ተቋም ነው።