ኮፕ 32 ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ላይ ያላትን ተሰሚነት እንደሚያሳድግ ተጠቁሟል
የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ትኩረት ከሚሰጣቸውና የዘመናችንን ዕጣ ፈንታ ከሚወስኑ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ ነው። የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ተደጋጋሚ ምክክሮችን ከማድረግ ቦዝኖ አያውቅም፤ ምንም እንኳን በሚፈለገው ልክ ውጤት መጥቷል ማለት ባይቻልም። ከእነዚህ መድረኮች መካከል የኮንፈረንስ ኦፍ ፓርቲስ (COP) ጉባኤ አንዱ ነው። ኢትዮጵያም 32ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP-32) እንድታዘጋጅ መመረጧ ለሀገሪቱ ትልቅ ክብር ብቻም ሳይሆን አዳዲስ የዲፕሎማሲ ዕድሎችን ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል።
በወርሃ ህዳር 2018 ዓ.ም በብራዚል ቤሌም የኮፕ-30 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተደርጓል። በዚህ ጉባኤ ከሁለት ዓመት በኋላም በሺህዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚታደሙበትን የ“ኮፕ-32” የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ተመርጣለች። የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ኢትዮጵያ ይህን ጉባኤ እንድታዘጋጅ መመረጧ፣ ኮፕ-32ን ማስተናገድ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ላይ ያላትን ተሰሚነት እንደሚጨምረው፣ የውጭ ግንኙነት እና ዓለም አቀፍ ገጽታዋን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሳድገው ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን ተናግረዋል።
የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ዴያሞ ዳሌዴጋ፣ የኢትዮጵያ መመረጥ ያጋጣሚ ወይም የዕድል ጉዳይ እንዳልሆነ ተናግረዋል። በዚህ ወቅት የሰው ልጆች ህልውና ስጋት ከሆኑ ዓለም አቀፍ ችግሮች መካከል አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን ያወሱት ምሁሩ፣ “ኢትዮጵያ ይህን ችግር በሚቀርፉ የመፍትሄ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች፣ እያደረገችም ትገኛለች። ለአብነትም በየዓመቱ በርካታ ችግኞችን ትተክላለች። አረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት ላይ በመመስረት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራችም ነው። እነዚህ ሥራዎች ደግሞ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እያገኙ የመሆናቸው አንዱ ማሳያ ይህን ጉባኤ እንድታዘጋጅ መመረጧ ነው” ብለዋል።
ይህ ጉባኤ በርካታ ሀገራትን የሚያሰባስብና ዓለም አቀፍ ተቋማትን የሚያሳትፍ መሆኑን የተናገሩት ምሁሩ፣ “የጊዜው የሰው ልጅ ህልውና ጥያቄ በመሆኑ ኢትዮጵያ ይህን ዕድል ማግኘቷ በአንድ በኩል የዲፕሎማሲ ድል ነው። በአረንጓዴ አሻራ ላይ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ዕውቅና ማግኘታቸውን ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ በቀጣይ በአዲስ አበባ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን አቋም ለሌሎች ሀገራት ለማስረዳት፣ ተጽዕኖዋንም ይበልጥ ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት” ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግስታት በአስተዳደር፣ ድህነትና ዘላቂ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) በዚሁ ጉዳይ ላይ ቀደም ብሎ ለአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል በሰጡት አስተያየት፣ ጉባኤውን ለማስተናገድ ኢትዮጵያ የተመረጠችው በአፍሪካ ትልቅ የህዝብ ቁጥርና አቅም ካላት ናይጀሪያ ጋር ተወዳድራ ነው። ለዚህም ያበቃት የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳን ቀዳሚ አድርጋ በመስራቷ ነው። በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት በአረንጓዴ አሻራ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ በመትከል የተገኘ ውጤት ነው። ከዚህ ባሻገር አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ከተማ፣ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን የምትወክል በመሆኗ ኢትዮጵያ ጉባኤውን የማዘጋጀት እድል እንድታገኝ አድርጓታል ብለዋል።
ይህንን ጉባኤ ለማዘጋጀት በኢትዮጵያ በኩል የሚደረገው ዝግጅት፤ ለተሳታፊዎች የተሻለ አገልግሎት ማቅረብ እና የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ዝግጁነትን ማሳደግ ነው። በቀጣይ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚቋቋሙበትና ጥናትና ምርምር የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚፈጥር ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለአስተናጋጅነት መመረጧ፣ ከራሷም አልፎ የአፍሪካን ወሳኝ ፍላጎቶች በባለቤትነት ይዛ ለማቅረብ ትልቅ አጋጣሚ እንደሆነ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ዴያሞ አብራርተዋል። ምሁሩ አክለውም አዲስ አበባ እያከናወነቻቸው ያሉ የልማት ሥራዎች እንደ ኮፕ 32 ያሉ ታላላቅ ጉባኤዎችን ለማዘጋጀት አቅም እየፈጠረላት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኮፕ 32ን ምክንያት በማድረግ የበርካታ ሀገራት የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ። ይህም አዲስ አበባ እንደ አፍሪካ የዲፕሎማሲ መቀመጫነቷ የዓለምን ትኩረት በላቀ ደረጃ እንድትስብ ያደርጋል። የኮፕ ጉባኤ ከዚህ ቀደም ያዘጋጁ ሀገራትን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ፣ ጉባኤው ለኢትዮጵያ መልከ ብዙ ዕድሎችን ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል። የኮፕ ጉባኤዎች ለአየር ንብረት ለውጥ የሚውለውን የገንዘብ ድጋፍ የሚወስኑ ዋና መድረኮች ናቸው። ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እቅዷን በማጉላት፣ ለትግበራ የሚያስፈልገውን ዓለም አቀፍ የገንዘብና የቴክኖሎጂ ድጋፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከወዲሁ በማዘጋጀት የመጠየቅና የማስፈጸም ዕድል ይኖራታል። እንዲሁም የአፍሪካን አጠቃላይ አቋም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር በማሰናሰል የመሪነት ሚና መወጣት ትችላለች። ይህን ሚና በአግባቡ ለመወጣት ከወዲሁ ዝግጅቶች እየተካሄዱ እንዳለ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት አፍሪካን በሚገባ የሚወክል ኮፕ 32 ጉባኤ ለማዘጋጀት እንዴት ተቀራርበው መስራት እንደሚችሉ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እና ከቡድናቸው ጋር ውይይት አድርገዋል። በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ መሪነት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮፕ-32ን የተሳካ ለማድረግ የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር ለመሆን ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም ባለፈው ሳምንት በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከኡራኤል እስከ ብራስ፣ ከቦሌ መድኃኔዓለም-ጎላጎል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና የፒኮክ (ማዕከላዊ) ፓርክ ግንባታን እንቅስቃሴ በመስክ በጎበኙበት ወቅት “ኢትዮጵያ የዓለምን ትኩረት የሚስበውን የኮፕ 32 ጉባኤ የምታስተናግድ መሆኗ እድለኛ…” መሆኗን በመግለጽ፣ ለጉባኤው ከወዲሁ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል። በኮሪደር ልማቱ የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ የሚከናወንበት አካባቢ አንዱ ጉባኤው የሚካሄድበት ማዕከል በመሆኑ አስቀድመዉ የተጀመሩ የኮሪደርና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት፣ “የኮፕ 32 ጉባኤ ከዓለም ዙሪያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች የሚታደሙበት በመሆኑ፣ ጉባኤው በአዲስ አበባ መዘጋጀቱ ከሀገር መልካም ገፅታ ግንባታ በተጨማሪ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገበያ ትስስር እንዲሁም መሰል ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ወደ ሀገራችን በቀጣይነት ለማምጣት ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። መላው የከተማችን ነዋሪዎችና የንግዱ ማህበረሰብ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ጉባኤው ይዞት የሚመጣውን መልካም ዕድል አሟጠን እንድንጠቀም፣ ለጉባኤው ስኬታማነትም ከወዲሁ ሁላችንም ዝግጅት እንድናደርግ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የኮፕ 32 ጉባኤን በአዲስ አበባ ማስተናገድ ለኢትዮጵያ ታላቅ የዲፕሎማሲ ዕድል እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን በአጽንኦት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የዓለም መሪዎችን በመሰብሰብ የአፍሪካን አጀንዳ በመያዝ የመሪነት ሚና የምትጫወትበት እንደሚሆን የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮ መነሻ በማድረግ አብራርተዋል። የሀገር ገጽታዋን በማሳደግ እና ለኢኮኖሚ ልማት የሚያግዙ ስምምነቶችን በመፈረም ከዚህ ጉባኤ ከፍተኛውን የዲፕሎማሲ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትርፍ ልታገኝ እንደምትችልም ጠቅሰዋል። ይህ ጉባኤ እንዲሳካ ከወዲሁ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመጥቀስ፣ የአገልግሎት ተቋማት ለዓለም አቀፉ ጉባኤ በሚመጥን መልኩ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ከወዲሁ የአቅም ግንባታ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው አሳስበዋል። በእርግጥ ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ በመዲናዋ ተደርጎ እንዲጠናቀቅ የማድረግ ሥራ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም። የግል ዘርፉና የከተማዋ ነዋሪዎችም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በአብርሃም ገብሬ