ብሔራዊ ገዢ ትርክትን በትውልዱ ውስጥ ለማስረጽ በሚደረገው ጥረት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ግንባር ቀደም ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባ ተገለጸ።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ “በመደመር መንግሥት እይታ አሰባሳቢ ገዢ ትርክት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ከሸገር ከተማ የፉሪ ክፍለ ከተማ ጋር የወዳጅነት ስፖርታዊ ጨዋታ አካሂዷል።
በሁለቱ ክፍለ ከተሞች የሥራ ኃላፊዎች መካከል የተደረገው ይህ የወዳጅነት ጨዋታ፣ በዋናነት በገዢ ትርክት ግንባታ ሂደት ውስጥ አመራሩ ለትውልዱ አርዓያ መሆን እንዳለበት ዓላማ ያደረገ መሆኑን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መብራቱ ደሴ ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም፣ ከስፖርታዊ መድረኩ ባሻገር ወጣቱን በኪነ-ጥበብና በተለያዩ የጋራ ልማት ሥራዎች በማገናኘት አንድነቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በመግለጽ ይህም በጋራ ለሚሠሩ ሥራዎች ስኬታማነት የላቀ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።
የፉሪ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አለኬ ዋቆ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ መሰል መድረኮች ከመገፋፋት ይልቅ እንደ አንድ አካል በማሰብ ለጋራ ዕድገት ለመሥራት ዕድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

መድረኩን በአመራሮች መካከል የሥራ መደላድል ከመፍጠር ባለፈ፣ በትውልዱ ላይ የሚፈጥረው በጎ ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
የስፖርታዊ ጨዋታው የወንድማማችነት ስሜታቸውን እንዳጎለበተው የገለጹት ተሳታፊዎቹ በቀጣይም ብሔራዊ ገዢ ትርክትን በትውልዱ ዘንድ ለማስረጽና በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በሔኖክ ዘነበ