AMN – ሐምሌ 25/2018 ዓ.ም

ለ2ኛ ጊዜ እየተከናወነ ያለው የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሠራተኞች እና አመራሮች ስፖርታዊ ፌስቲቫል የማጠቃለያ መርሐ-ግብር እየተካሄደ ይገኛል።
በምኒልክ አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተከናወነ በሚገኘው በዚህ መርሐ-ግብር ላይ በርካታ የተቋሙ አመራሮች እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የቴሌቪዥን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጥላሁን ካሳ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሠራተኛው ጤንነቱን ጠብቆ በሥራው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ታስቦ ስፖርታዊ ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱ አስረድተዋል፡፡
ተቋሙ የትውልድ ድምፅነቱን ለማረጋገጥ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡

ጤንነታችንን፣ አንድነታችንን እና መተጋገዝን ይበልጥ የሚያዳብረውን ስፖርታዊ ፌስቲቫል አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አመላክተዋል፡፡
በመርሐ-ግብሩ የብዙኃን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን፤ በአመራሮች መካከልም አዝናኝ የእግር ኳስ ጨዋታ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል በቴሌቪዥን እና በኢንጂነሪንግ ዘርፎች መካከል የፍጻሜ የእግር ኳስ ጨዋታ የሚከናወን ይሆናል፡፡