19ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ሲጀምር በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ እና ሦስተኛ ላይ የተቀመጡ ቡድኖች ያገናኛሉ።
አርሰናል ከ አስቶንቪላ በ15ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር በቪላ ፓርክ ተገናኝተው የማይረሳ ፉክክር አስመልክተዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የዋና ዳኛው ፊሽካ እየተጠበቀ ኤሚ ቡንዲያ ግብ አስቆጥሮ አስቶንቪላን ለፈንጠዚያ አርሰናልን ለሀዘን የዳረገበት አጋጣሚ ስሜቱ አሁንም ትኩስ ነው።
አርሰናል ከቪላው ሽንፈት በኋላ ሦስት የሊግ ጨዋታዎችን በተከታታይ በማሸነፍ መሪነቱን አስጠብቋል። አስቶንቪላም በተመሳሳይ የድል ጉዞ ላይ ይገኛል። በተለይ በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎቹ ማንችስተር ዩናይትድ እና ቼልሲን ማሸነፉ የቡድኑን እውነተኛ ተፎካካሪነት አሳይቷል።
በሁሉም ውድድሮች ያደረጋቸውን 11 የመጨረሻ ጨዋታ በድል ማጠናቀቁ የቡድኑ አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬን አስወድሷል። ዛሬ ምሽት 5:15 በኤምሬትስ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ ለሁለቱም ክለቦች ወሳኝ ነው።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ካሸነፈ ከዋነኛ የዋንጫ ተፎካካሪዎቹ አንዱን ወደ ኋላ የሚያስቀርበት እድል ይሰጠዋል። በአንፃሩ አስቶንቪላ ካሸነፈ ከአርሰናል ጋር በነጥብ ተስተካክሎ እውነተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑን ለዓለም ያሳያል።
ሁለቱ ክለቦች በመጨረሻ ባደረጓቸው አምስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሦስቱን ያሸነፈው አስቶንቪላ ነው። መድፈኞቹ አንድ ድል ሲያስመዘግቡ በአንዱ ነጥብ ተጋርተዋል።
በዛሬው ፍልሚያ በአርሰናል በኩል ብራይተንን በረቱበት ጨዋታ ያልተሳተፉት ዩሪያን ቲምበር እና ሪካርዶ ካላፊዮሪ መግባታቸው አልተረጋገጠም። አስቶንቪላ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ማቲ ካሽ እና አማካዩ ቡባካር ካማራን በቅጣት መጠቀም አይችልም። በጉጉት የሚጠበቀውን ጨዋታ ዳረን ኢንግላንድ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሸዋንግዛው ግርማ