ሞሮኮ እና ማሊ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፉ

You are currently viewing ሞሮኮ እና ማሊ ወደ ቀጣዩ ዙር አለፉ

AMN ታኅሣሥ 21 ቀን 2018 ዓ.ም

በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጇ ሞሮኮ ዛምቢያን በማሸነፍ የጥሎ ማለፍ ዙሩን ተቀላቅላለች። በልዑል ሞሌይ አብደላ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሞሮኮ በአስደናቂ ብቃት 3ለ0 አሸንፋለች።

አዩብ ኤል ካቢ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በውድድሩ ያስመዘገባቸውን ግቦች ሦስት አድርሷል። የ32 ዓመቱ የኦሎምፒያኮስ አጥቂ በተለይ በመቀስ ምት ያስቆጠረው ግብ ግሩም ነበር።

ተጫዋቹ በተመሳሳይ ሁኔታ ኮሞሮስ ላይ ኳስ እና መረብ ማገናኘቱ ይታወሳል። ሌላኛውን የሞሮኮ ግብ ብራሂም ዲያዝ ማስቆጠር ችሏል።

የሪያል ማድሪዱ ተጫዋች የውድድሩ ሦስተኛ ግቡ ሆኖም ተመዝግቧል። ካከናወነቻቸው ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ የያዘችው ሞሮኮ ምድብ አንድን በበላይነት አጠናቃለች።

በጨዋታው ከጉዳቱ ያገገመው አችራፍ ሃኪሚ ተቀይሮ በመግባት ተጫውቷል። በዚሁ ምድብ በተደረገ ሌላ ጨዋታ ማሊ ከኮሞሮስ 0ለ0 ተለያይተዋል።

በጨዋታው አማካዩ አማዱ ሃይዳራን በቀይ ካርድ ያጣችው ማሊ በሦስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ሞሮኮን ተከትላ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅላለች።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review