ጤናማ አመጋገብ – ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አስተማማኝ ጋሻ!

You are currently viewing ጤናማ አመጋገብ – ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አስተማማኝ ጋሻ!
  • Post category:ጤና

AMN- ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም

ጤናማ አመጋገብ ሲባል ማህበረሰቡ በየዕድሜ ክልሉ ከሚመገበው ምግብ ማግኘት የሚገባውን ንጥረ ነገሮች ማግኘት መቻል መሆኑን የሥነ-ምግብ ህክምና ባለሙያ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርት የሆኑት ዶክተር ዘላለም ደበበ ይገልፃሉ፡፡

ሰውነታችን በሚገባ ሥራውን መሥራት እንዲችል በቂ ጉልበት ማግኘት ያስፈልገዋል ያሉት ባለሙያዋ፣ ጤናማ አመጋገብ በተለይም ጉልበት የሚሰጡ ሦስት ዋና ዋና የሚባሉ ገንቢ ምግቦች (ፕሮቲን፣ ቅባት እና ካርቦሃይድሬት እንዲሁም በቂ ቪታሚኖችን) የያዘ ሊሆን እንደሚገባው ያስረዳሉ፡፡

አመጋገብ ጤናማ የሚሆነው ብቁ፣ ንጹህ እና እነዚህን ሁሉ ንጥረ ነገሮች በየዕድሜ ክልሉ በበቂ ሁኔታ ሲቀርብ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ምግብ አብዛኛውን ጊዜ የተቀናጀው በየአካባቢው፣ በየባህሉ እና በየሀገሩ የተለያየ ምንጭ ሊኖረው እንደሚችል በማንሳትም፣ ነገር ግን ከውስጡ የሚገኘው ነገር ተመሳሳይ ስለመሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

ከእነዚህ የምግብ ዓይነቶች ውስጥም ጉልበት ሰጪ ስለሆኑ ከእህል የሚመደቡ እንደ እንጀራና ቂጣ እንዲሁም ሥራ ሥሮች እንሰትና ቦይና ያሉ ምግቦች በምግብ ሳህናችን አንድ አራተኛውን ሊይዙ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

ገንቢ የሆኑና እንደ ማባያ የምንጠቀማቸውን ከጥራጥሬ የሚገኙ ምግቦች እንደ ምስር፣ አተር፣ ያሉ ወይም ከእንሰሳት ተዋፅኦ የሚገኙ እንደ ሥጋ፣ ዶሮ፣ ዓሣ፣ እንቁላል ያሉት በትንሽ ቅባት በመስራት መመገብ እንደሚገባም ያነሳሉ፡፡

እህል፣ ቅባት እና ገንቢ የምንላቸው የምግብ ዓይነቶች በማዕዳችን ካሉ፣ ተጨማሪ ማዕድንና ቪታሚን የሚሰጡን አትክልት እና ፍራፍሬ ደግሞ በምግብ ሳህናችን ግማሽ ያህሉን መያዝ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ይህንንም እንደየ ሰዉ በቀን ሁለቴም ሆነ ሦስቴ በበቂ ሁኔታ ከበቂ ፈሳሽ ጋር አቀናጅቶ መመገብ ከተቻለ ጤናማ ምግብን በመመገብ ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች እራስን መጠበቅ ይቻላል በማለት አብራርተዋል፡፡

የጨው እና የስኳር አጠቃቀምን በተመለከተም፣ አንድ ሰው ስኳር በቀን ከ5 የሻይ ማንኪያ ያልበለጠ፣ ጨው ደግሞ ከአንድ ድርበብ የሻይ ማንኪያ በላይ መጠቀም እንደሌለበት ዶክተር ዘላለም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቂ የሆነ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል የሚሉት ባለሙያዋ፣ ሰዎች እንደየሥራቸው ባህሪ በቀን ለ30 ደቂቃ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በቂ ፈሳሽ መውሰድ፣ ማረፍ እና በቂ እንቅልፍ ማግኘትም ጤናን ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review