ከኢንዞ ማሬስካ ጋር ትናንት በስምምነት የተለያየው ቼልሲ ምትክ አሰልጣኝ እያፈላለገ ነው፡፡
የምዕራብ ለንደኑ ክለብ የስትራስቡርጉ ሊያም ሮሴኒአር ቀዳሚ ምርጫው ስለመሆኑ ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል፡፡ በደቡብ ለንደን የተወለደው ሊያም ሮሴኒአር በግራ ተከላካይ ስፍራ ብራይተንን ጨምሮ ለበርካታ ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ ሬዲንግ ፣ ሃል ሲቲ ፣ ፉልሃም እና ኢፕስዊች ታወን ሌሎች ተጫውቶ ያሳለፈባቸው ክለቦች ናቸው፡፡
ለእንግሊዝ ከ20 እና 21 ዓመት በታች በድምሩ 11 ጨዋታዎችን ማድረግም ችሏል፡፡ ለአባቱ ሀገር ሴራሊዮን ለመጫወት ጥያቄ ማቅረቡም የሚታወስ ነው፡፡
ሮሴኒአር በ2018 ጫማውን ከሰቀለ በኋላ የአሰልጣኝነት ስልጠና ወስዶ በብራይተን ምክትል አሰልጣኝነትና ከ23 ዓመት በታች ቡድን በዋና አሰልጣኝነት ሰርቷል፡፡ ከዚያም በደርቢ ካውንቲ ምክትል አሰልጣኝነት ስራ ጀመረ፡፡ ይሁን እንጂ ዋና አሰልጣኝ የነበረው ፊሊፕ ኮኩ ሲሰናበት በጊዜያዊ ኃላፊነት ተሾመ፡፡

ዋይኒ ሩኒ በዋና አሰልጣኝነት ክለቡን ሲረከብ በድጋሚ ወደ ምክትል አሰልጣኝነት ወርዶ መስራት ጀመረ፡፡ ደርቢ ካውንቲን ለቆ ከ161 በላይ ጨዋታዎችን ላደረገው ኸል ሲቲ ዋና አሰልጣኝነት ፊርማውን አኖረ፡፡
ክለቡ በሻምፒዮንሺፕ ሰባተኛ ሆኖ በማጠናቀቁና ከፕሪምየር ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ውጭ በመሆኑ ነበር ከሁለት ዓመታት ገደማ በኋላ ከኃላፊነት የተሰናበተው፡፡ ሐምሌ 2024 የፓትሪክ ቪየራ ምትክ ሆኖ ከትውልድ ሀገሩ ወጥቶ የፈረንሳዩን ስትራስቡርግ ተረከበ፡፡
በክለቡ ባሳየው ተስፋ ሰጪ ውጤት እስከ 2028 የሚያቆየውን ውል የተፈራረመው ሊያም ሮሴኒአር፤ በቼልሲ በጥብቅ እየተፈለገ ይገኛል፡፡
ባለፈው ዓመት ስትራስቡርግ በሊግ አንድ ሰባተኛ ሆኖ አጠናቆ ለዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ እንዲያልፍ ያደረገው የ41 ዓመቱ ሊያም ሮሴኒአር ፣ የኢንዞ ማሬስካ ምትክ የመሆን እድሉ ሰፊ መሆኑን ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት እያወሩት ነው፡፡
በታምራት አበራ