የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የሻቢያ መንግስት ከኢትዮጵያ የውስጥ ባንዳዎች እና ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ የፅንፈኛው ፋኖ ቡድንን ለማስታጠቅ በስውር የላከውን ከ56 ሺህ በላይ የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥይቶችን ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በወልዲያ የፍተሻ ጣቢያ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጿል፡፡
እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ በተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ጥይቶቹ በሻቢያ መንግስት እንደተላኩና ጽንፈኛው ሕወሃት በትግራይ ክልል መቀሌ ላይ ተቀብሎ ወደ አማራ ክልል ሸዋሮቢት በማስገባት ለጽንፈኛው ፋኖ ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ተረጋግጧል።

ለሻቢያ መንግስት ድልድይ ሆኖ እየሠራ ያለው ፅንፈኛው የህወሃት ቡድን ፅንፈኛው ፋኖን በማስታጠቅ የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ አቅዶ ከኤርትራ በመቀሌ በኩል በስውር የላከውን 41,999 የክላሽ ጥይት፣ 14,000 የብሬን ጥይት እና 800 የድሽቃ ጥይት በአጠቃላይ 56,799 ጥይቶች በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አ.አ B94744 የጭነት አይሱዙ ተሽከርካሪ ከሲሚንቶና ከብሎኬት ጋር አመሳስሎ በመጫን በአማራ ክልል ወልዲያ ከተማ አድርገው ወደ ሸዋሮቢት ለማስገባት ሲያጓጉዙ በወልዲያ የፍተሻ ጣቢያ ላይ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጠንካራ ክትትልና ፍተሻ ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራባቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

ባዳዎች እና ባንዳዎች ተቀናጅተው የሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስ ሀገራችን እያካሄደች ያለችውን ልማትና ዕድገት ለማደናቀፍ በተለያዩ ጊዜ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወቃል። አሁን ላይም እነዚህ የጠላት ኃይሎች በሀገራችን ላይ አደጋ ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው የፀጥታ ኃይሉ የጀመረውን ኦፕሬሽን አጠናከሮ እንደሚቀጥል እየገለፀ ኅብረተሰቡም ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር የተለመደውን ድጋፍ እንዲያደርግ ሲል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ ጥሪውን አቅርቧል።