AMN ሐምሌ 11/2018
በትግራይ ክልል ያለው አስከፊ ቀውስ በአስቸኳይ እንዲቆም የሠላም ጥሪ ቀረበ።
በትግራይ ሰላም እና ለውጥ ምክርቤት የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ይገኛል።
የሠላማዊ ሠልፉ ተሳታፊዎችም ህገወጡ የህወሃት ቡድን በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለዉ አፈናና የጦርነት ዝግጅት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ሰልፈኞቹ ጦርነት ይበቃል: የአለም እና የፌደራል መንግስት የህገወጡን ቡድን እንቅስቃሴ በትኩረት ሊያጤን ይገባል ብለዋል።
የፕሪቶሪያ የሠላም ስምምነት ትግበራ ቀጣይነት እንዲኖረዉ የጠየቁት ሠልፈኞቹ በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥም ጠይቀዋል።
አለም አቀፍ እና ሃገራዊ የሰብአዊ መብቶች እና ህጎችን በመጣስ የሚደረገውን የወጣቶች ህገወጥ አፈሳንም ተቃዉመዋል።
የትግራይ ሰላም እና ለውጥ ምክርቤት የጠራው ሰልፍ በትግራይ ያለውን ሁሉን አቀፍ ቀውስ እና ህዝቡን ከብተና እና አላስፈላጊ እልቂት ለመከላከል ያለመ መሆኑን የምክርቤቱ ሚዲያ አመራር አቶ ብርሃኔ ገብረየሱስ ለኤኤምኤን ገልፀዋል።

የጦርነቱ አስከፊ ጉዳት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢቋጭም ተግባራዊ እንዳይሆን “ቡድኑ” እያሰናከለ መቆየቱ ሳያንስ ህጋዊ መንግስትን ፈንቅለው ህዝቡን ቁም ስቅል እያሳዩ እና የጦርነት ዝግጅት እያደረጉ ነው ብለዋል።
ቡድኑ ተላላኪ እና የትርምስ ባህሪ ያለዉ ነው ሲሉ የገለፁት አቶ ብርሃኔ ወጣቶችን በመሸጥ ለጦርነት እየዳረጋቸዉ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል።
በመሃመድ ፋንታዉ