ኩዊንስ ሱፐርማርኬቶች ስያሜያቸውን ወደ ዓለም አቀፉ የፈረንሳይ ኩባንያ ካርፉር ብራንድ ሊቀይሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ስያሜያቸውን ወደ ካርፉር የሚቀይሩት የመጀመሪያዎቹ የሜድሮክ የኩዊንስ ሱፐርማርኬት ቅርንጫፎች እስከ ሰኔ ስራ እንደሚጀምሩ ተገልጿል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከካርፉር ጋር የፈጠረው የስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት የፍራንቻይዝ እና የአቅርቦት አጋርነትን እንደሚያጠቃልል በጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ተጠቅሷል።
በሚድሮክ ስር ከሚገኙ በርካታ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ኩዊንስ ሱፐርማርኬት የመጀመሪያ መደብሩን የከፈተው ከስምንት ዓመት በፊት በ2010 ዓ.ም ነበር። በአሁኑ ሰዓት ኩዊንስ ሱፐርማርኬት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 13 ቅርንጫፎች አሉት።

የሁለቱ አካላት ስምምነት ያሉትን የኩዊንስን ሱፐርማርኬቶች ስያሜ ከመቀየር ባሻገር አዲስ ቅርንጫፎችን መክፈትንም እንደሚያካትት የካርፉር የዓለም አቀፍ አጋርነት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፓርትሪክ ላስፈርጉስ ገልፀዋል። ስምምነቱ የሀገር ውስጥ ሸማቾችን በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርቶችን ለዓለም ገበያ እንዲቀርቡ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያስችላልም ብለዋል። የኢትዮጵያ ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ በማቅረብ ለሸማቾች ዘመናዊ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ለሀገር በቀል ምርቶች ትልቅ ዕድል እንደሚሰጥም ተገልጿል።
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የካርፉርን ምርጥ ተሞክሮዎች ለማምጣትና ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች ጥራት ያላቸው እና ተመጣጣኝ ምርቶችን እንዲሁም ፍላጎታቸውን በትክክል የሚያሟላ አገልግሎት ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልፀዋል።

የመጀመሪያዎቹ መደብሮች እስከ 2026 የመጀመሪያ አጋማሽ ድረስ የንግድ ስያሜያቸውን የሚቀይሩ ሲሆን እስከ ሰኔ 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ሥራ እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል። የካርፉር እና ሚድሮክ ስምምነት በኢትዮጵያ የችርቻሮ ንግድ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን እንደሚፈጥር እና ለተጠቃሚዎች ሰፊ አማራጭን ይዞ ይመጣል የሚል እምነት እንዳለውም ኮሚሽኑ አስታውቋል።
መንግስት ለኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ብቻ ክፍት ሆነው የቆዩት የጅምላ እና ችርቻሮ ንግድ ዘርፎች ላይ የውጭ ሀገር ባለሀብቶችም እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያ በመጋቢት 2016 ዓ.ም ማውጣቱ ይታወሳል። ይህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አካል ሲሆን ለእንደነዚህ አይነት አለማቀፍ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ መግባት በር ከፍቷል። ኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶችን ቀልብ እየሳበች ስለመሆኑም አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።

ካርፉር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ40 በላይ ሀገራት ዘንድ ተደራሽ ነው። በነዚህ ሀገራትም ከ15ሺ በላይ መደብሮች አሉት። ባለፈው በ2024 ብቻ 94.6 ቢሊዮን ዩሮ የሽያጭ መጠን ያስመዘገበ ግዙፍ ተቋም መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ይታያል አጥናፉ