የፅንስ መቋረጥ እንዴት ይከሰታል?

You are currently viewing የፅንስ መቋረጥ እንዴት ይከሰታል?
  • Post category:ጤና

AMN – ጥር 15/2018 ዓ/ም

ተደጋጋሚ የሚከሰት የፅንስ መቋረጥ በአለም አቀፍ ደረጃ እናቶችን ለአካላዊ ህመም ብቻ ሳይሆን ለከፍተኛ ስነ-ልቦናዊ ጫና የሚዳርግ ችግር ነው፡፡

በተከታታይ ሁለት ጊዜ እና ከዚያ በላይ የፅንስ መቋረጥ ሲያጋጥም ጉዳዩ ጥልቅ የህክምና ምርመራ የሚያስፈልገው መሆኑን በአበበች ጎበና የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ዶ/ር አህመድ አባቡ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።

ዶ/ር አህመድ እንደገለጹት፤ የፅንስ መቋረጥ በዘፈቀደ የሚከሰት ሳይሆን ግልጽ የሆኑ የጤና እክሎች ውጤት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ ለሚከሰቱ የፅንስ መቋረጦች 60 በመቶ የሚሆነው ምክንያት የጄኔቲክ ወይም የክሮሞዞም ቁጥርና ቅርፅ መዛባት መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ ችግር አብዛኛውን ጊዜ በወላጆች ጤና ላይ በሚኖር ችግር ሳይሆን፣ ፅንሱ በሚፈጠርበት ቅጽበት በሚከሰት የሴል ክፍፍል ስህተት የሚመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የማህፀን ጤና ለፅንሱ እድገት ወሳኝ መሆኑን ያብራሩት ስፔሻሊስቱ፤ የማህፀን ተፈጥሯዊና መዋቅራዊ ችግሮች ሌላኛው መንስኤ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ፅንሱ በቂ የደም ዝውውር በማያገኝበት የማህፀን ግድግዳ ላይ ሲያርፍ፣ በማህፀን ውስጥኛው ክፍል የሚገኙ እጢዎች መኖር እና ፅንሱ እያደገ ሲመጣ ክብደቱን መሸከም የማይችል የማህፀን በር መላላት ለተደጋጋሚ የፅንስ መቋረጥ የሚያጋልጡ ዋና ዋና ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

የሰውነት መከላከያ ስርአት ፅንሱን እንደ ባዕድ ነገር በመቁጠር ጥቃት ሊያደርስ ይችላል ያሉት ዶ/ር አህመድ፤ በተለይም አንቲ-ፎስፎሊፒድ ሲንድረም የተባለው የጤና ሁኔታ ወደ ፅንሱ የሚሄዱ የደም ስሮች እንዲረጉ በማድረግ ፅንሱ አየርና ምግብ እንዳያገኝ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

የሆርሞን እና የውስጥ ደዌ ችግሮች መኖር፤ ያልተስተካከለ የታይሮይድ እጢ ሆርሞን፣የፕሮጄስትሮን ሆርሞን ማነስ እና የስኳር በሽታ ለፅንስ መቋረጥ ቀጥተኛ መንስኤዎች መሆናቸውንም ገልፀዋል።

ችግሩ በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸው ጥንዶች ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ሳይንሳዊ የምርመራ ሂደቶችን መከተል እንዳለባቸው ባለሙያው ይመክራሉ።

ከእነዚህም መካከል የወላጆችን የዘር ህዋሳት መመርመር፣ የማህፀን ቅርፅና ቱቦዎች ክፍት መሆናቸውን ማረጋገጥ እና በደም ውስጥ ፅንሱን የሚጎዱ ፀረ-እንግዳ አካላት መኖራቸውን የሚያረጋግጥ የደም ምርመራ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።

ተደጋጋሚ የፅንስ መቋረጥ ያጋጠማቸው እናቶች ጤናማ ልጅ የመውለድ እድላቸው አሁንም ሰፊ መሆኑን ያበሰሩት ዶ/ር አህመድ፤ ሂደቱ በትዕግስትና በቅርብ የህክምና ክትትል መታገዝ እንዳለበት አሳስበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም እንደ ሲጋራ፣ አልኮል እና ከመጠን ያለፈ የካፌይን አጠቃቀምን መቀነስ ለተሳካ እርግዝና ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ ሲሆን፤ ሆኖም ግን በዚህ ሙሉ በሙሉ ችግሩን መቅረፍ እንደማይቻል ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review