AMN መስከረም 13/2019
የኢትዮጵያ አስተማማኝ የባህር በር ማግኘት የቀጣናውን ሀገራት የጋራ ዕድገትና ትብብር እንደሚያጠናክር ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኒው ዮርክ መካሄዱን ቀጥሏል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ማምሻውን በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ንግግር አደርገዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር በር ሳይኖር ዘላቂ ልማት ማምጣት እንደማይቻል ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ባህር በር የማግኘት ጉዳይ ለሁሉም የቀጣናው ሀገራት ከሚያስገኘው የጋራ ጥቅም እና ዕድገት ጠቀሜታ አንጻር መመልከት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎቷን እውን ለማድረግና ከዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ጋር ለመተሳሰር ሁሉንም የዲፕሎማሲ አማራጮች ተጠቅማ እየሰራች መሆኑን አመልክተዋል።