AMN መስከረም 13/2019
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ከኢንተርናሽናል ክራይሰስ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ኮምፈርት ኢሮ ጋር መክረዋል።
81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኒው ዮርክ መካሄዱን ቀጥሏል።
“መተማመንን ዳግም መገንባት እና አዳዲስ ለውጦችን በአግባቡ መምራት፣ ለሁሉም የሚሰራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መፍጠር” የጠቅላላ ጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።
በፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከኢንተርናሽናል ክራይሰስ ግሩፕ ድርጅት ፕሬዝዳንት ኮምፈርት ኢሮ ጋር ውይይት አድርገዋል።
ሁለቱ ወገኖች በሀገራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች በተለይም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ባላት ሚና ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።
በተጨማሪም በውይይቱ ኢትዮጵያ በሱዳን ሰላምና መረጋጋት የማስፈን ጥረቶች ላይ ያላትን አስተዋጽኦ ላይ ምክክር መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ ከ81ኛው ተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በሁለትዮሽና የባለብዙወገን መድረኮች ላይ እየተሳተፈች ሲሆን ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስከብሩና የአፍሪካ ፍላጎቶች በሚያስከብሩ አጀንዳዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ይገኛል።