ኮሌጆቹ በኢንተርፕራይዞቻቸው አማካኝነት ከፍተኛ ገቢ ማመንጨት ጀምረዋል
የሠው ኃይል፣ ካፒታል እና መሬት እነዚህ ሦስቱ የዕድገት ቁልፍ አቅሞች እንደሆኑ የምጣኔ ሃብት ጠበብቶች ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ ሃሳባቸው ትክክል ስለመሆኑም ተጨባጭ ምሳሌዎችን ለመጥቀስ አይቸገሩም፡፡ ባለጸጋ የሆኑ ግለሰቦችን፣ ድርጅቶችን (ተቋማትን)፣ ሀገራትን በመዘርዘር የመበልፀጋቸው ምስጢር ሦስቱን ቁልፍ አቅሞች በብቃትና በተቀናጀ መልኩ ከመጠቀም የመጣ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በእርግጥ እነዚህን ቁልፍ አቅሞች ይዘው በድህነት አጥር ውስጥ “ተመቻችተው የተቀመጡ” እንዳሉ አይካድም። ለእንደነዚህ ዓይነቱ ነው “የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው…” የመሳሰሉ ሀገርኛ ተረቶች የተነገረው፡። ምክንያቱም፤ ድህነት ሞቋቸው ወይም ተለማምደውት የሚኖሩት፣ ያላቸውን ቁልፍ አቅሞች አውቀው፣ አቀናጅተው፣ ወደ ጥቅም ካልለወጧቸው፤ አቅሞቹ በራሳቸው ዕድገትን አያመጡም፡፡
ጥቅል የሆነውን እሳቤ ተንተን አድርገን ለመረዳት የቴክኒክና ሙያ ተቋሞቻችንን በምሳሌነት መመልከት ጥሩ ይሆናል። የቴክኒክና ሙያ ተቋማት መጠኑ ይለያይ እንጂ ከላይ የጠቀስናቸውን ሦስት አቅሞች የያዙ ናቸው፡፡ የሠው ኃይላቸውን ብንመለከት፤ በዕውቀት፣ በክህሎት እና በልምድ የዳበረ ነው፡፡ ካፒታላቸውን ያየን እንደሆን፤ መንግስት በጀት የሚበጅትላቸው፣ አነሰም በዛም የውስጥ ገቢ የሚያገኙ፣ በገንዘብ ቢተመኑ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ቴክኖሎጂዎችን (ማሽኖችን) አቅፈው የያዙ ወርክሾፖች ያሏቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ያላቸው ይዞታ ስለ መሬት ችግር ለማንሳት የማይመች ነው፡፡ በአግባቡ ጥቅም ላይ ቢውልና ቢለማ “ሀገር መደገፍ የሚችል ነው” ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ የሆነው ሆኖ እነዚህ ተቋማት፤ “የተሰጠን ተልዕኮ ሰልጣኞችን ተቀብሎ፣ በተለያየ ሙያ አሰልጥኖ፣ ማስመረቅ ነው” በሚል የተፃፈ ተልዕኮ ውስጥ ተሸፍነው አቅሞቻቸውን አቀናጅተው ጥቅም ላይ ሳያውሏቸው ቆይተዋል፡፡ በዚህም ከመንግስት በጀት ጥገኝነት ሳይላቀቁ፣ ለብዙሃኑ ዕድገት ተምሳሌትነታቸውን በተግባር ሳይገልጡ፣ ሙያተኞችን ስለማፍራታቸው በተጨባጭ ምርት ወይም አገልግሎት ሞክረው ሳያሳዩ… እስካሁን ቆይተዋል። ከመቅረት መዘግየት ይሻላልና አሁን ላይ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት መነቃቃት ጀምረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ካሉ የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት መካከል ወደ አንጋፋዎቹ የአዲስ አበባ ተግባረዕድ ፖሊ ቴክኒክ እና ጀነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች በማቅናት ከመደበኛው ሙያተኞችን ከማሰልጠን ሥራ ባሻገር፤ ያላቸውን ውስጣዊ አቅሞች ለመጠቀም እያደረጉ ያለውን ጅምር ጥረት እና ውጤት ለመመልከት ችለናል፡፡ በምልከታችንም ኮሌጆቹ፤ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ የምርትና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን ማቋቋማቸውን፣ ባቋቋሟቸው የንግድ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ማቅረብ መጀመራቸውን፣ በዚህም ለተቋማቸው ተጨማሪ ገቢ ማስገኘታቸውን፣ ከሁሉም በላይ ከተቋም እስከ ሀገር ሊሰፋ በሚችል የዕድገትና ብልፅግና ጉዞ ውስጥ አይተኬ አስተዋፅኦ ማሳረፍ የሚያስችላቸውን መሰረት እየገነቡ መሆናቸውን ተረድተናል፡፡
አቶ ተስፋዬ አድማሱ፤ የአዲስ አበባ ተግባረዕድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ናቸው፡፡ በኮሌጃቸው ተቋቁሞ ምርትና አገልግሎት በማቅረብ ላይ ስለሚገኘው የአዲስ አበባ ተግባረዕድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት (ኢንተርፕራይዝ) ዝርዝር መረጃ አጋርተውናል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ ድርጅቱ ለትርፍ የተቋቋመ ነው። ለመመስረቱ ዋና ምክንያት በፌደራል ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ሥራና ክህሎት ቢሮ ተዘጋጅቶ የወረደ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሚመሩበት ስትራቴጂ እና መመሪያ ሲሆን፤ እያንዳንዱ የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ተቋም የውስጥ አቅሙንና ፀጋውን በመጠቀም ምርትና አገልግሎት ማቅረብ የሚችል ድርጅት (ኢንተርፕራይዝ) ማቋቋም እንዳለበት የሚያስገድድ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ኮሌጁ ኢንተርፕራይዙን የማቋቋም ሥራ በ2016 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ አካባቢ በማቋቋም ሕጋዊ ፍቃድን አገኘ፡፡ ከዚያም አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን በማከናወን በ2017 በጀት ዓመት ሕዳር ወር መጨረሻ አካባቢ ወደ ማምረት ሥራው ገባ፡፡
እንደ ዲኑ ገለፃ፤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጁ አስር ዘርፎች ላይ ምርትና አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችለውን ፍቃድ አውጥቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-
ከእንጨት የሚሠሩ የቤትና ቢሮ ዕቃዎችን፣ የብረታ ብረት ሥራ ውጤቶችን፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ሶፍትዌር ማበልፀግ)፣ በባዮሜዲካል ዘርፍ (የሕክምና መሣሪያዎች ጥገናና ማማከር)፣ የተሽከርካሪ ጥገና (ጋራዥ)፣ የአሽከርካሪ ስልጠና፣ የውሃ መስመር ዝርጋታና ጥገና ሥራ፣ የሕንጻ ግንባታ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ምርትና አገልግሎቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የእንጨት እና የብረታ ብረት ሥራ ውጤቶች፣ በባዮሜዲካል ዘርፍ (የሕክምና መሣሪያዎች ጥገናና ማማከር)፣ የሕንጻ ግንባታ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ለኢንተርፕራይዙ ገቢ በሚያስገኝ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌሎችንም በተሻለ ሁኔታ ለማንቀሳቀስ እየተሠራ ነው፡፡
በተመሳሳይ የጀነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ “ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት” አቋቁሞ የራሱን ገቢ ማመንጨት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው ቀደም ብሎ ነበር። ይሁን እንጂ በመንግስት ተቋም ውስጥ ያሉ አሠራሮች ለዚህ ምቹ ባለመሆናቸው የሚጠበቅበትን ያክል እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችል መቆየቱን ያስታወሱት በኮሌጁ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ አበጀ በለጠ፤ በቅርቡ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የወጣው አዲስ መመሪያ፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ከመደበኛው የማሠልጠን ሚናቸው በተጓዳኝ የውስጥ አቅማቸውን በገቢ የሚያሳድጉበትን መንገድ የሚቀይስ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ራሱን የቻለ ለትርፍ የተቋቋመ ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት በመመስረት ኮሌጁ ቀድሞ የጀማመረው ሥራ ፍሬያማ የሚሆንበት መልካም አጋጣሚ በማግኘት ወደ ተጠናከረ ተግባር መግባቱን ገልፀዋል፡፡
ኮሌጁ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት ለማቋቋም ያለፈባቸውን ሂደቶች በተመለከተ ሥራ አስኪያጁ ሲያብራሩ፤ “ሕጋዊ ሂደቶችን በመከተል፣ ከንግድ ፈቃድ ማውጣት ጀምሮ ደረሰኝ የማሳተም፣ በጀት የመመደብ፣ ግብዓት የማሟላት … ተግባራትን በመፈፀም ሥራውን በ2015 በጀት ዓመት በመደበኛነት ጀመርን፡፡ ስንጀምር የኢንተርፕራይዙ መነሻ ካፒታል 100 ሺህ ብር ብቻ ነበር፡፡ በዚሁ በጀት ዓመት በተሠራው ሥራ 700 ሺህ ብር ትርፍ ተገኘ፡፡ ከዚያም በ2016 በጀት ዓመት ካፒታሉን ወደ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በማሳደግ የተለያዩ ሥራዎችን አጠናክረን አስቀጠልን፡፡ አሁን ላይ የኢንተርፕራይዙ (ድርጅቱ) በካፒታል ደረጃ 10 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ2018 በጀት ዓመትም ሥራዉን በማሳደግ ከ100 እስከ 150 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ አጠቃላይ ገቢን ለማግኘት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡” ብለዋል፡፡
በፖሊቴክኒክ ኮሌጆቹ የተቋቋሙት ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅቶች (ኢንተርፕራይዞች) ምርትና አገልግሎታቸውን ከኮሌጁ ጀምረው ለመንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት፣ ለድርጅቶች፣ ለግለሰቦች ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የማኑፋክቸሪንግ ክፍል አሰልጣኝ እና የኮሌጅ ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን አየለ፤ ምርትና አገልግሎታቸውን በስፋትና በጥራት እያዳረሱ መሆኑን ጠቁመዋል። እንደሳቸው ማብራሪያ ከሆነ፤ ኢንተርፕራይዙ ከተቋቋመ ጊዜ በኋላ በሠራቸው ሥራዎች ለልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ለቢሮ አገልግሎት የሚውል 150 ሼልፎችን አምርቶ አቅርቧል፡፡ በአራዳ እና በቦሌ አገልግሎት መስጠት ለጀመሩት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ቢሮዎች ሙሉ የእንጨት ምርት ውጤቶችን ሠርቶ አቅርቧል፡፡ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችን (በኮሌጁ የተሠራውን እና ለኢንተርፕራይዙ የተሸጋገረውን የሲኤንሲ ፕላዝማ በመጠቀም በጥራትና በፍጥነት አምርቶ አቅርቧል፤ በቦታም በመገኘት በባለሙያዎች ገጥሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፤ ከቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት አስተዳዳር በመጣ የአርሶ አደር መሬት ልኬት ሥራ ላይ የኮሌጁ የሰርቬይንግ እና ድራፍቲንግ አሰልጣኞች እና ሰልጣኞች ተሳትፈዋል። የአዲስ አበባ ተግባረዕድ እና የዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች በጋራ በመሆን በከተማ አስተዳደሩ ስር ያለውን የምርታማነት የልህቀት ማዕከልን ባለ አራት ወለል ሁለት ሕንፃዎችን የማሻሻል እና በግብዓት የማሟላት ሥራን ውል ወስደው ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ በከተማዋ ለሚገኙ የጤና ተቋማት የሕክምና መሣሪያዎች ጥገናና የማማከር አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ በዚህም በትንሽ ብልሽት ተቀምጠው የነበሩ ትላልቅ የሕክምና መሣሪያዎችን ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡
በጀነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅት ከሚያቀርባቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች መካከል፡- የእንሰሳት መኖ ማቀነባበርና ማምረት፣ አጠቃላይ የሕንጻ ግንባታ፣ የእንጨት የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ የብረታ ብረት ሥራ ውጤቶች፣ የንፅህና መጠበቂያዎች (የፈሳሽና ጠጣር ሳሙናዎች)፣ የአረንጓዴ ልማት (ችግኝ ማፍላት እና ማስዋብ) ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን የጠቀሱት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አበጀ፤ ከምርትና አገልግታቸው ተጠቃሚዎች መካከል አንዱ ለሆነው ኮሌጃቸው ለሥራቸው የሚጠይቁት ገንዘብ በውጭ አቅም ከሚሠራው በ10 ከመቶ የዋጋ ቅናሽ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ እና ግለሰቦች ሌሎቹ የኢንተርፕራይዙ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ለማሳያነትም፤ በ2017 በጀት ዓመት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የእንጨት የቢሮ ዕቃዎችን አምርተው ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ በጥቅሉ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘታቸውንም አስረድተዋል፡፡
በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች የተቋቋሙት ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅቶች (ኢንተርፕራይዞች) ገና ከጅምሩ ለተቋማቸው፣ ለአሰልጣኝና ሰልጣኞች፣ ለአካባቢያቸው እና ለከተማ አስተዳደሩ ላቅ ያለ ጠቀሜታ በማስገኘት ላይ ናቸው፡፡ ያነጋገርናቸው የሥራ ኃላፊዎች እንዳብራሩት፣ ኢንተርፕራይዞቹ ሥራ በመጀመራቸው፤ ለተቋማት፣ ለድርጅቶች፣ ለህብረተሰቡ ጥራት ያላቸውን ምርትና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ተችሏል። ኮሌጆች የውስጥ ገቢያቸውን የሚያሳድጉበትን ውጤታማ አማራጭ ፈጥሯል፡፡ አሠልጣኞች ከስልጠና ሰዓት (ከ11፡30) በኋላ ያለውን ትርፍ ጊዜ በሥራ ላይ በማዋል፣ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ ከሥራ ቦታቸው ርቀው ሳይሄዱ፣ ተጨማሪ ሥራ የሚሰሩበት ሁኔታ በመፈጠሩ፤ በመደበኛውም ሆነ በትርፍ ጊዜ ሥራቸው ደስተኛና ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ የኮሌጁ ሠራተኞች በረጅም ጊዜ ክፍያ የተለያዩ የቤት ዕቃዎችን በማሠራት እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ በብልሽት እና መሰል ምክንያቶች ያለ አገልግሎት ለዓመታት የተቀመጡ ማሽኖች አስፈላጊው ጥገና በማድረግ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
በተጨማሪም፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅቶች (ኢንተርፕራይዞች) አቋቁመው ወደ ሥራ መግባታቸው አሰልጣኝና ሰልጣኞች ያላቸውን ዕምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ውጤት እንዲለውጡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ በዚህም አዳዲስ እና ውጤታማ ቴክኖሎጂዎች በራስ አቅም ተሰርተው በኢንተርፕራይዞች የምርትና አገልግሎት እሴት መጨመር ላይ አስተዋፅኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህንን በተመለከተ የጽሑፋችን ማዕከል ባደረግናቸው ሁለት ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች ውስጥ በሥራ ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን እናንሳ፡፡ በአዲስ አበባ ተግባረዕድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኞች የተሠራው የሲኤንሲ ፕላዝማ ማሽን እንዲሁም በጀነራል ዊንጌት ፖሊቴክኒክ አሰልጣኞች የለማው የመኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ለኢንተርፕራይዞቹ ተሸጋግረው ከፍተኛ አበርክቶ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
የቴክኒክና ሙያ ተቋማቱ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅቶች (ኢንተርፕራይዞች) ከጅምሩ እየሠሩት ያለው ስራ ተስፋ ሰጪ ውጤት በማስገኘት ላይ ነው፡፡ ጅምራቸው ተጠናክሮና ሰፍቶ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ምክንያቱም የድርጅቶቹ (ኢንተርፕራይዞቹ) ዓላማ ብዙ ነው። የመጀመሪያው ዓላማ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆችና ተቋማት በዋናነት ከሚያከናውኑት የማሰልጠን ተግባር በተጓዳኝ ገቢ በሚያስገኝ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ማስቻል፣ ገቢያቸውን ማሳደግ፣ በሂደትም ከመንግስት በጀት ጥገኝነት ማላቀቅ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ የስልጠና ጥራትን ማሳደግ ሲሆን፤ ይህም ሰልጣኞች ከዚህ ቀደም በኮሌጆች የሰለጠኗቸውን ሙያዎች በተግባር የተደገፈ ልምምድ ለማድረግ ወደ ሌሎች ኢንዱስትሪዎች እና ኢንተርፕራይዞ ይሄዱ የነበረበትን ሁኔታ በማስቀረት በቅጥር ግቢው ውስጥ በአግባቡ የተግባር ላይ ልምምድ የሚያደርጉበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ አሠልጣኞች ከስልጠና ሰዓት (ከ11፡30) በኋላ ያለውን ትርፍ ጊዜ በሥራ ላይ እንዲያውሉ፣ ተጨማሪ ገቢም እንዲያገኙ የማስቻል ዓላማንም ይዟል፡፡ ለምርት እና አገልግሎት መሻሻል የሚያግዙ ወይም እሴት የሚጨምሩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ዕውን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ሰልጣኞች በሙያቸው ተቀጣሪ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችል አስተሳሰብ እንዲገነቡ የላቀ ሚና አለው፡፡ ይህንን ማሳካት እንደሚቻል ከጅምሩ እየታየ ያለው ውጤት ይጠቁማል፡፡
ስለዚህ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተቋቋሙ ባለአንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ ድርጅቶች (ኢንተርፕራይዞች) ውጤታማ እንዲሆኑ መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች የአዲስ አበባ ተግባረዕድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ተስፋዬ አድማሱ ባስተላለፉት መልዕክት ጽሑፋችን እንቋጫለን። ዋና ዲኑ እንዳሉት፤ ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛዎች ያለን ግንዛቤ አሁን ካለበት ደረጃ የበለጠ መሻሻል አለበት። በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በአስተሳሰብ የዳበሩ ሥራ ፈጣሪ ትንታግ ዜጎች የሚፈልቁበት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አጭር ዕድሜ ያለው የአገራችን ልምድም ሆነ፤ አሁን በከፍተኛ ዕድገት ላይ የሚገኙት የጀርመን፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር እና መሰል አገራት የተሞክሮ ምስጢር የሚያሳየን ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ስለሆነም የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋሞቻችንን አቅም በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡
በደረጀ ታደሰ