ልጆች፤ መንገድ ስትሻገሩ ምን ምንጥንቃቄዎችን ታደርጋላችሁ?

You are currently viewing ልጆች፤ መንገድ ስትሻገሩ ምን ምንጥንቃቄዎችን ታደርጋላችሁ?

ልጆች፤ እንዴት ናችሁ? ስለትራፊክ አደጋ ምንነት እና ስለሚያስከትለው ጉዳት ግንዛቤ ይኖራችኋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ እንደምታውቁ አንጠራጠርም፡፡ ይህን እንድንል መነሻ የሆነን ያነጋገርናቸው ልጆች የሰጡት አስተያየት ነው፤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡   

ፍሬሕይወት አበራ እባላለሁ። የልዕልት ዘነበ ወርቅ መታሰቢያ ትምህርት ቤት ተማሪ ነኝ፡፡ ትምህርት ቤት ስሄድም ሆነ በሰፈር ስንቀሳቀስ ከትራፊክ አደጋ ራሴን እጠብቃለሁ። አስፓልት የምሻገረው ቀኝና ግራዬን አይቼ፣ በእግረኛ መንገድ ማቋረጫ (ዜብራ) ነው፡፡ በሩጫ ሳይሆን ተረጋግቼ ከሰዎች ጋር አብሬ እሄዳለሁ። ከሶስቱ የትራፊክ መብራት ቀዩ ሲበራ እግረኛ መሄድ እንዳለበት እና አረንጓዴ ሲበራ ተሽከርካሪ  እንደሚያልፍ ስለማውቅ ይኼንኑ ተግባራዊ አደርጋለሁ። በዚህም ችግር ገጥሞኝ አያውቅም፡፡

በአሁኑ ወቅት ራሴን ችዬ መሻገር እችላለሁ፡፡ ስሻገርም ከጓደኞቼ ጋር አልላፋም፤ አልጫወትም፤ ተቃቅፌም አልሄድም፡፡ ከዚህ በፊት ትምህርት ቤት ቤተሰቦቼ ሲያሻግሩኝ እነዚህን ጥንቃቄዎች ማድረግ እንዳለብኝ ይነግሩኝ ስለነበር ተግባራዊ አደርጋለሁ፡፡ እነዚህን ጥንቃቄዎች ማድረጌ ራሴን ከትራፊክ አደጋ እንድጠብቅ አድርጎኛል፡፡

አቤኔዘር አንዷለም እባላለሁ፡፡ የግቢ ገብርኤል ትምህርት ቤት ተማሪ ነኝ።  ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ራሴን ከትራፊክ አደጋ እጠብቃለሁ፡፡ የትራፊክ አደጋ ለሞት የሚያደርስ መሆኑን ወላጆቼ ስለሚነግሩኝ፣ መምህራን ስለሚያስተምሩን እና በቴሌቪዥንም የደረሰ ጉዳት ስለማይ ጥንቃቄ አደርጋለሁ፡፡ ግራና ቀኜንም አይቼ በእግረኛ ማቋረጫ መንገድ ነው የማቋርጠው፡፡ ከእኔ በዕድሜ የሚያንሱ ጓደኞቼንም እጃቸውን ይዤ አሻግራቸዋለሁ፡፡

ስልክ መንገድ ላይ እያወሩ ማለፍ ተገቢ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ቀይ የትራፊክ መብራት ሲበራ አስፓልት አቋርጣለሁ። አረንጓዴ ሲበራ ደግሞ እቆማለሁ፡፡ ይህን የትራፊክ መብራት ማወቄ ጉዳት እንዳይደርስብኝ አድርጎኛል፡፡

እየሩስ ገሊላ እባላለሁ፡፡  የምማረው  በልዕልት ዘነበ ወርቅ መታሰቢያ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሁልጊዜም  አስፓልት ሳቋርጥ የእግረኛ መንገድ ያለበትን አይቼ ነው። የትራፊክ መብራቶችንም ጠንቅቄ ስለማውቅ ምንም ሳልቸገር አልፋለሁ። መኪናው ያለበትን እርቀት አያለሁ፡፡ እጄን ኪሴ ውስጥ አድርጌ፣ ጃንጥላ ዘርግቼ፣ የጆሮ ማዳመጫ አድርጌ እንዲሁም ስልክ እያወራሁ አስፓልት አላቋርጥም። በዚህም እስከ አሁን በሰላም ወጥቼ እየገባሁ ነው፡፡ የትራፊክ አደጋ አካልን ከማጉደል እስከ ሞት የሚያደርስ በመሆኑ ቤተሰቦቼና መምህራን የሚነግሩኝን ተግባር ላይ በማዋል በተቻለኝ መጠን ራሴን እጠብቃለሁ፡፡

ልጆች፤ ይኼን የልጆች የጥንቃቄ ተግባር እያነበባችሁ እኔስ ምን እያደረግኩ ነው? ብላችሁ ወደራሳችሁ እየተመለከታችሁ እንደሆነ ተስፋ አለኝ። አሁን ደግሞ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው ባለሙያ ያሉትን እናስነብባችሁ፡፡

ኢንስፔክተር ታምሩ ደግፈው እባላለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የህዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ክፍል ኃላፊ ነኝ፡፡ ልጆች በምትንቀሳቀሱበት ቦታ ሁሉ የመኪናን እንቅስቃሴ አይታችሁ በእግረኛ መንገድ መሻገር አለባችሁ፡፡ አስፓልቱን ከመሻገራችሁ በፊት ቆማችሁ መጀመሪያ ግራችሁን ከዚያም ቀኛችሁን በማየት ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ መኪና መቆሙን አይታችሁ መንገዱን አቋርጡ፡፡

በመንገድ ላይ ኳስ አለመጫወት፣ አለመላፋት፣ አለመተቃቀፍ፣ ተሽከርካሪ ላይ ተንጠልጥሎ አለመሄድ እንዲሁም በተሽከርካሪ ተከልላችሁ አለማቋረጥ ይጠበቅባችኋል፡፡ ወላጆቻችሁ፣ የትምህርት ቤት መምህራን እንዲሁም ታላላቆቻችሁ የሚመክሯችሁን ማዳመጥና ተግባራዊ ማድረግ አለባችሁ። ከጓደኞቻችሁ ጋር ተቃቅፋችሁና እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ መንገድ አታቋርጡ። የትምህርት ቤት ሰርቪሳችሁ ላይ እጆቻችሁንና ጭንቅላታችሁንም በመስኮት አታውጡ፡፡ ይህንን ካደረጋችሁ ራሳችሁን ከአደጋ ትጠብቃላችሁ፡፡

ልጆች፤ የትራፊክ አደጋ ከአካል መጎዳት እስከ ሞት ስለሚያደርስ ከዚህ ራሳችሁን ለመጠበቅ የምታደርጉትን የጥንቃቄ እርምጃ አጠናክራችሁ ቀጥሉ መልዕክታችን ነው፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review