የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት እውን አድርጓል – አቶ አሕመድ ሽዴ

AMN – ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም.

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትንና የወጪ ውጤታማነትን ማሻሻሉን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት ግዥና ንብረት አፈጻጸምና የ2019 ዕቅድን በተመለከተ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶችና የሀብት አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለፊስካል መረጋጋት፣ ለመንግሥት ወጪ ቅልጥፍና፣ ለግልጽነትና ተጠያቂነት መጠናከር የጎላ ስትራቴጂካዊ ሚና አለው።

የመንግሥት ግዥ የመንግሥት ፖሊሲ ወደ ተግባር የሚቀየርበት፣ የሕዝብ ሀብት በኃላፊነት የሚተዳደርበት፣ የአገልግሎት ጥራትን የሚያሻሽልና ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትንና የወጪ ውጤታማነትን ማሻሻል አስችሏል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመንግሥት የኤሌክትሮኒክ ግዥን በማስፋት፣ የግዥ ዝመናን በማጠናከር፣ ሕጎችና አሠራሮችን በማዘመን አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ ተቋማዊ አቅምን ከማጠናከር ባለፈ በመንግሥት ወጪ ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያጠናከሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግሥት ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለግብርና፣ ለውኃ፣ ለመሠረተ ልማት፣ ለዲጂታል ልማትና መሰል ዘርፎች የሚመድበው በጀት በመንግሥት ግዥ ወደ ተግባር፤ የልማት ፖሊሲ ወደ ውጤት የሚቀየርበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በኤሌክትሮኒክ ግዥ፣ በዲጂታላይዜሽንና በአሠራር ማሻሻያዎች ያስመዘገባቸው ውጤቶች በመንግሥት ወጪዎች ላይ ያለውን ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመንግሥት ግዥ ላይ የሚሻሻለው እያንዳንዱ ሂደት በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ውጤት የሚያመጣ መሆን አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል።

በ2019 በጀት ዓመት ሁሉም የፌዴራል ተቋማት የሚመሩበት መርህ ትክክለኛነት፣ ጥራትና ወቅታዊነት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የዲጂታል ሪፎርም የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ይደግፋል ብለዋል።

የዲጂታል ሽግግር አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በበጀት ዓመቱ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን በተሟላ ሁኔታ መጠቀም፣ የመንግሥትን ንብረት በዘመናዊ መንገድ ማስተዳደር እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የመንግሥት ሀብት የሕዝብ አደራ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸው፣ የሕዝብን አደራ በታማኝነት መጠበቅ የሁሉም የመንግሥት ተቋማት የመጀመሪያ ግዴታ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review