በአረንጓዴ ገጽታዋ የምትታወቀው የአፍሪካ መዲና – አዲስ አበባ

AMN ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም

በዓለም ላይ በአረንጓዴ ሽፋንና ገጽታቸው ከሚታወቁ ከተሞች መካከል ሲንጋፖር ፣ ኖርዌይ ፣ ከፐንሃገን ፣ ካናዳና ስዊድን በቀዳሚነት ይነሳሉ፡፡

ከተሞቹ በለምለም ጫካዎች ፣ በተፈጥሮ ፓርኮችና መናፈሻዎች ፣ በውሃ በተከበቡ አረንጓዴ አካባቢዎችና ተራራዎች ይታወቃሉ፡፡

እነዚህ ከተሞች የካርቦን ልቀትን በመቆጣጠርና በመቀነስ ፣ በታዳሽ ኃይል አጠቃቀም ፣ ሰፋፊ የብስክሌት እና የህዝብ መጓጓዣ መንገዶችን በመገንባት ፣ በከተማ ውስጥ ዛፎችንና አረንጓዴ ስፍራዎችን በማልማት እና በዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ የተሻለ ተሞክሮ አላቸው፡፡

የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የአለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ከጥቂት አመታት በፊት በተራቆቱና አካባቢዎችና ገጽታዋ ትታወቃለች፡፡

ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች በየቦታው የሚጣሉባት ፣ ወንዞቿ በእጅጉ የተበከሉ ፣ ጎዳናዎቿም ለህዝብ መጓጓዣና ለመዝናኛነት የማይመቹ ፣ በተሽከርካሪ ጭስ የታፈነችና አየሯም ለጤና የማይስማማ መዲና ነበረች፡፡

አዲስ አበባ ስያሜዋ የሚያምር ፣ አቀማመጧ የሚመች ፣ ወንዞችን ጨምሮ በተለያዩ የተፈጥሮ ጸጋዎች የታደለች መዲና ብትሆንም አጠቃላይ አካባቢዋና ገጽታዋ ግን ከስሟ ጋር ያልተጣጣመላት መዲና ሆና ለዓመታት ኖራለች፡፡

ዛሬ ላይ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራርነት በመላ ሃገሪቱ በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ፣ በኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማት አዲስ አበባ አዲስና አረንጓዴ ገጽታን ተላብሳለች፡፡

ወንዞቿ ለህዝብ መናፈሻነትና መዝናኛነት ውለዋል፤ ተራራዎቿ አረንጓዴና ለምለም ዛፎችን ለብሰዋል፤ ጎዳናዎቿ ለብስክሌት መጓጓዣነት ውለዋል ፣ ጭስም ድምጽም የሌላቸው ዘመናዊ ተሽከርካሪዎች የሚፈሱባት ዘመናዊ መዲና ሆናለች፡፡

አዲስ አበባ እንደሌሎች የዓለም ሃገራት በለምለም ጫካዎች ፣ በተፈጥሮ ፓርኮችና መናፈሻዎች ፣ በውሃ በተከበቡ አረንጓዴ አካባቢዎችና ተራራዎች የምትታወቅ የዓለማችን የቱሪዝም መዳረሻና መቆያ ለመሆን በቅታለች፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት 90 ሚሊዮን ችግኞች በመዲናዋ የተተከሉ መሆናቸውን እና የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋንም እጅግ ዝቅተኛ ከነበረበት 2.8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማለቱን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብሩ የተራቆቱ አካባቢዎች አረንጓዴ ለብሰዋል፤ የነጠፉ ወንዞች እና አካባቢዎች ማንሰራራት ችለዋል ፤ አዲስ አበባ ንፁህ ፣ ውብ ፣ ለመኖር ምቹ እና የቱሪስት ማዕከል መሆን ችላለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የምንተክለው ተስፋን ፣ ልማትን ፣ ልምላሜን ፣ ጥላን ፣ ምግባችንን ብሎም ብልፅግናን ነው ያሉት ከንቲባዋ የምንተክለው ለዛሬ ጥቅማችን ብቻ ሳይሆን ለትውልድ እዳን ሳይሆን የልምላሜና የብልፅግና ምንዳን ለማውረስ ነው ማለታቸውም መዲናዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ምቹ ከተማ ለማድረግ የታዘውን ራዕይ በተግባር የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review