AMN- ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እና በአህጉሩ የምትጫወተው ግንባር ቀደም ሚና፣ የአንድነትና የትብብር ማዕከልነቷን በግልጽ እንድገነዘብ ረድተውኛል ሲሉ የአዘርባጃን ሪፐብሊክ ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ (ፕ/ር) ሳሂባ ጋፋሮቫ ገለጹ።
አፈ-ጉባኤ ሳሂባ ጋፋሮቫ (ፕ/ር) በውጭ ጉዳይ ኢንስትቲዩት በተዘጋጀ በፓርላመንታሪ የዲፕሎሚሲ እና የባለብዙ ወገን ውይይት ላይ እንደተናገሩት፣ የአዘርባጃንና የኢትዮጵያ ግንኙነት በፈጣን ሁኔታ እየተጠናከረ መጥቷል።

አፈ-ጉባኤዋ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ጋር ፍሬያማ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።
እነዚህ ውይይቶች ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ እና በአህጉሩ የምትጫወተውን ግንባር ቀደም ሚና፣ የአንድነትና የትብብር ማዕከልነቷን በግልጽ እንድገነዘብ ረድተውኛል ብለዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የከፍተኛ አመራሮች ግንኙነት እየጎለበተ መምጣቱንም አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዘርባጃን ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ከፕሬዚዳንት ኢልሃም አሊዬቭ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በአዘርባጃን ጉብኝት ማድረጋቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት እያደገ ስመለምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።
የሄይዳር አሊዬቭ ፋውንዴሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሌይላ አሊዬቫ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የባህል እና ሰብዓዊ ትስስሩን ማጠናከሩን አሳታውሰዋል።
በኢትዮጵያ ፍላጎት እና አቅም ላይ ተመስርቶ የበለጸገውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተዘዋውረው መጎብኘታቸውንም ጨምረው ጠቅሰዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ኢትዮጵያ የራሷ ስኬት እና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ያደረገችው ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ የምትገኝና በአህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ መድረክ የምትጫወተው ሚና የሚደነቅ መሆኑን ማስታወቃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።