AMN- ጥር 16/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ኢትዮጵያን በአፍሪካ አህጉር ቀደምት የአየር ኃይል ባለቤት ከሆኑ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ማድረጉን የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ፡፡
ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ የኢፌዴሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዓሉ ያለፉትን ዓመታት የምናስታውስበት ብቻ ሳይሆን፣ ለዘጠኝ አሰርት ዓመታት ለሀገር የተበረከተ የጽናት፣ የአየር ላይ ጥበቃ እና የማይበገር ጥራት መገለጫ ነው ብለዋል።
ላለፉት 90 ዓመታት አየር ኃይላችን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር፣ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በመሳተፍ እና ሀገራዊ ፈተናዎችን በመመከት የሰማይ ጋሻ ሆኖ መቆየቱንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያን በአፍሪካ አሕጉር ቀደምት የአየር ኃይል ባለቤት ከሆኑ ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ማድረጉን ገልጸዋል ሌተናል ጄኔራሉ።
ጥቁር አንበሳ የአየር ትርዒት የኩራታችን እና የኤሮኖቲክስ ጥበባችን መገለጫ ነው ያሉት ዋና አዛዡ፣ የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች፣ የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ኩባንያዎች መሪዎች እና አጋሮች በትርዒቱ ላይ መገኘታቸው ይህንን መድረክ ወደ ዓለም አቀፍ የአንድነት እና የትብብር መድረክ ከፍ አድርጎታል ብለዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አየር ኃይል እና አየር መከላከያ ለሰጡት ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
የአየር ትርዒቶች መዝናኛዎች ብቻ እንዳልሆኑ በማንሳትም፣ እነዚህ ትርዒቶች የሀገርን ምናብ የሚያነቃቁ፣ ወጣት እጩ መኮንኖች እንዲፈጠሩ፣ ተማሪዎች አዳዲስ ግኝቶችን እንዲፈጥሩ እና ዜጎች በሀገራቸው የቴክኖሎጂ መጻዒ ዕድል ላይ ዕምነት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ስትራቴጂካዊ መሳሪያዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ዛሬ በሰማይ ላይ የምናያቸው አውሮፕላኖች የአፈጻጸም ብቃታቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን፣ ወደ አምስተኛ ትውልድ የአየር ኃይል ብቃት እና ወደ ዓለም አቀፍ አጋርነት የሚደረገውን ጉዞም እንደሚያሳዩ አንስተዋል።
ለዚህ ስኬት እንቅልፍ አጥተው ለደከሙ አብራሪዎች፣ ቴክኒሻኖች እና የደኅንነት ባለሙያዎች በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በታምራት ቢሻው