AMN ሐምሌ 27/2018

የአረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያን የወደፊት ተስፋ በማለምለም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መከላከል ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ስኬታማ ልማት መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተመካካሪ የዲያስፖራ አባላት ገለጹ።
“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሐሳብ የሚካሄደው የ800 ሚሊዮን የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዛሬ ከማለዳው 12፡00 ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ እየተካሄደ ይገኛል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለመመካከር ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የዲያስፖራ አባላትም በዛሬው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በመሳተፍ አሻራቸውን አኑረዋል።
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ተመካካሪ የዲያስፖራ አባላት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ታሪካዊና ሀገራዊ በሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፋቸው ሀገራዊ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራቸውን ያኖሩት ፓስተር አረጋ ሽፈራው፤ ዓለም በሙቀት መጨመር እየተፈተነች ባለችበት ወቅት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን እየተከለች መሆኗን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የበረሃማነትን መስፋፋትን በመግታትና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስረድተዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለቀጣይ ትውልድ ትልቅ አርዓያ የሚሆን ተሻጋሪ ድል መሆኑን ደግሞ ማሜ ወርቁ ገልጸዋል።
መትከልና ተክሎ ማሳደግ ትልቅ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ የተተከሉ ችግኞችን በዘላቂነት መንከባከብ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ ኡስታዝ ሙክታር ጀማል በኢትዮጵያ ከተከናወኑ ታላላቅ ለውጦች መካከል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ ጉልህ ሀገራዊ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ችግኝ በመትከል አሻራውን እያኖረ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ነዋዊ ሙሳ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ለአየር ንብረት መሻሻል ከፍተኛ ጥቅም ያለውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተደነቀ ያለ ተነሳሽነት መሆኑን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ተስፋን የሚፈነጥቅና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።