የቻይና ሳውዘርን ፓወር ግሪድ ቴክኖሎጂ እና የኤዳን ኤሌክትሮ ፓወር ግሩፕ ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማዕከል የማድረግ ዓላማን የሰነቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሰረቱ

You are currently viewing የቻይና ሳውዘርን ፓወር ግሪድ ቴክኖሎጂ እና የኤዳን ኤሌክትሮ ፓወር ግሩፕ ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማዕከል የማድረግ ዓላማን የሰነቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሰረቱ

AMN ጥር 18/2018

የአጋርነት ስምምነቱን የኤዳን ኤሌክትሮ ፓወር ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እድሪስ አደም እና የቻይና ሳውዘርን ፓወር ግሪድ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ከፍተኛ ተወካይ ዣኦ ዚዪ ተፈራርመዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዘመናዊ መልክ ለጀመረችው ኢኮኖሚያዊ ሽግግር አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ኃይል የኢንዱስትሪ ልማት ሞተር ብቻ ሳይሆን፣ ለዲጂታል ኢትዮጵያ ግንባታ መሰረት መሆኑን ገልጸው፤ ያለ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፈጠራን ማስፋፋትም ሆነ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እንደማይችልም ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በብሔራዊ የኃይል መስመር ላይ ብቻ ጥገኛ ሳትሆን ሚኒ-ግሪድ እና ሃይብሪድ የታዳሽ ኃይል ሥርዓቶችን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ይህም በገጠር የሚገኙ ስራ ፈጣሪዎችና ማህበረሰቦችም እኩል የዲጂታል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በኤዳን ኤሌክትሮ ፓወር ግሩፕ እና በቻይና ሳውዘርን ፓወር ግሪድ ቴክኖሎጂ መካከል የተመሰረተው አጋርነት ዘመናዊ የኃይል ማከፋፈያና ማከማቻ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ያስችላል ብለዋል።

የኃይል መፍትሔ መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ የመገጣጠምና የማምረት አቅምን ለማሳደግ እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ ስልጠና ለመስጠት ዕድል እንደሚፈጥርም ነው የገለፁት።

የሀገር ውስጥ አቅምን ለመገንባት ለሚሰሩ ኩባንያዎች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል።

የኤዳን ኤሌክትሮ ፓወር ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እድሪስ አደም በበኩላቸው፣ ኤዳን ፓወር በኢትዮጵያ የሀይል እድገት ውስጥ ለ20 ዓመታት አጋር ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።

ስምምነቱ የኢትዮጵያን ፍላጎት ለማሟላት፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት በጋራ ለመስራት ትልቅ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።

የቻይና ሳውዘርን ፓወር ግሪድ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ከፍተኛ ተወካይ ዣኦ ዚዪ እንዳሉት፣ይህ አጋርነት የቻይናን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም የሚያስችል ነዉ ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review