የአሜሪካዉ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የአቭዬሽን ኤክስፖ ጎበኙ
AMN ጥር 19 ቀን 2018 ዓ.ም
የአሜሪካዉ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የአቭዬሽን ኤክስፖ ጎብኝተዋል፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው እና የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የአቭዬሽን ኤክስፖ ጎብኝተዋል።
በዚህ ኤክስፖ አየር ኃይልን ጨምሮ የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ ፣መከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ፣ የመከላከያ ዩኒቨርስቲ እና ሌሎችም አለም አቀፍ ደርጅቶች ምርቶቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል።
በኤክስፖው የቀረቡት ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ውጤቶች የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ስኬት የሚያሳዩ ስለመሆናቸው ተጠቁሟል።
የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው ከጉብኝቱ በኋላ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀበባል ምስጋና አቅርበው፤ ኢትዮጵያ በመገኘታቸው ክብር እንደሚሠማቸው ገልፀዋል። በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጠልም ተናግረዋል።
የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን በበኩላቸው ለቀጠናው ሰላም በተለይም እንደ አልሸባብ እና አይኤስኤስ ያሉ ሽብረተኞችን ለመከላከል እና ለመደምሰስ በጋራ እንሰራለን ማለታቸዉን የሃገር መከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡