39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና የአፍሪካ ጣልያን ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የፌደራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ

You are currently viewing 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና የአፍሪካ ጣልያን ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የፌደራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ

AMN – ጥር 20/2018 ዓ.ም

39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና የአፍሪካ ጣልያን ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የፌደራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ።

የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በየዓመቱ በመዲናችን አዲስ አበባ ሲካሄድ መላው የከተማዋ ነዋሪዎች በፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና እንግዳ ተቀባይነትን ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍና ትብብር ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉርና ሀገር አቀፋዊ የጸጥታ ሁኔታ ትንተናን መነሻ ያደረገው የፌደራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና የአፍሪካ ጣልያን ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቅድመ- ዝግጅት በማጠናቀቅ ስምሪት ሠጥቶ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከዚህ ቀደም ከምናደርጋቸው ዝግጅቶች ለየት ባለ መልኩ ከጉባኤው ጎን ለጎን የአፍሪካ ጣልያን ጉባኤ የሚደረግ በመሆኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ በሁለቱም ጉባኤዎች የሚሳተፉ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችን እና ሌሎች እንግዶችን ተቀብላ ስታስተናግድ በተሰጣት ኃላፊነት እና በተጣለባት እምነት ልክ እንግዶቿ በከተማዋና ከከተማ ውጭ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ደህንነታቸውን መጠበቅ እና ማረጋገጥ ከፀጥታ አካላቱ እንደሚጠበቅ ያሳሰቡት የፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ ሲሆኑ ይህንኑ የሚመጥን በቂ ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ያለፈው የጥምቀትና የከተራ በዓል በስኬት እና በድምቀት መጠናቀቁ ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን ሁሉም በየደረጃው ያለው አመራርና አባላት ባከናወኑት ጠንካራ ስምሪት ነው ያሉት የአዲስ አበባ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ከፊታችን ያለውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና የአፍሪካ ጣልያን ጉባኤ በስኬት ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የከተማችን ነዋሪና የሠላም ሠራዊቱ በስራው ላይ በንቃት ተሳታፊ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የህብረቱንና የጣልያን አፍሪካ ጉባኤ ለመካፈል የሚመጡ እንግዶች በሆቴሎች፣ በመዝናኛ እና በገበያ ስፍራዎችና በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ናቸው።

አያይዘዉም የፀጥታ ኃይሉ የሚያከናውነው ተግባር በቴክኖሎጂ የሚደገፍ መሆኑን ጠቁመው፣ የፀጥታ ኃይሉን ተግባር በተባባሪነት መንፈስ በመደገፍ ነዋሪዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እና ከፀጥታ አካላቱ ጋር ተቀናጅተው በመስራት እንደ ወትሮው ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል።

በስብሰባው ላይ የተገኙ የየስራ ክፍሉ ኃላፊዎች በበኩላቸው የህብረቱ ጉባኤና የጣልያን አፍሪካ ጉባኤ በሚጠበቀው ልክ እንዲከናወን ሁሉም በተሠጠው ስምሪት መሠረት ሊንቀሳቀስ ይገባልም ብለዋል።

በተለይም በአጀብ ስራ ላይ መንገዶች ዝግ በሚደረጉበት ወቅት አሽከርካሪዎች እና እግረኞች በትዕግስት በመጠበቅ ወይም ሌሎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም በሀገር ገፅታ ግንባታው ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የፌደራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ጥሪውን አቅርቧል ።

ህብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙም በነጻ የስልክ መስመሮች 990፣ 991፣ 987፣ 816 እንዲሁም በ011-1-26-43-59፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በእጅ ስልኮች የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (Citizen Engagement Application) EFPApp በመጠቀም ጥቆማ መስጠት እንደሚገባም የጋራ ግብረ ሃይሉ ጥሪውን አስተላለፏል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review