AMN- ግንቦት 3/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋትና ወጣቶችን በዘርፉ በማብቃት ረገድ የተጀመሩ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋ ሰሞኑን ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ኩነቶች ማዕከል እየሆነች መጥታለች ብለዋል።
የከተማዋን የስፖርት አቅርቦት ለማሳደግና በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የተቀረጹት የግንባታና የሥልጠና መርሐ ግብሮችም በስኬት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ማህበረሰቡ በየመኖሪያ አካባቢው የስፖርት አማራጮችን እንዲያገኝ በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ ቀደም ሲል በከተማዋ የነበሩት 495 የስፖርት ሜዳዎች በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ከ2 ሺህ በላይ እንዲደርስ ተደርጓል።

ከአካባቢ ሜዳዎች ባለፈ የከተማዋን ገጽታ የሚቀይሩና ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች መዳረሻ የሚሆኑ ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ ሲሆኑ፣ ለአብነትም የአቃቂ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ግንባታ ማጠናቀቂያ ደረጃ ላይ መድረሱና የታደሱት የአዲስ አበባ፣ የአደይ አበባ እና የአበበ ቢቂላ ስታዲየሞች ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸው ተጠቅሷል።
እነዚህ መሠረተ ልማቶች ኢትዮጵያ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅሟን በእጅጉ እንደሚያሳድጉላትም ከንቲባዋ አክለው ገልጸዋል።
የከተማዋን የቱሪዝም መስህብነት ከመጨመርና የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ባለፈው ግንቦት ወር ብቻ አራት ታላላቅ ዓለም አቀፍ ስፖርታዊ ኩነቶች በመዲናዋ ተስተናግደዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የ‘ግራንድ ፕሪ’ የጎዳና ላይ ሩጫ፣ የሼክ ዛይድ የበጎ አድራጎት ሩጫ፣ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የሲቲ ማውንቴን ባይክ ውድድር እና የምስራቅ አፍሪካ የእጅ ኳስ ውድድር የኢትዮጵያን ባህል ለዓለም ለማስተዋወቅና ለዜጎች የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
በሌላ በኩል በአሸናፊነት ስነ-ልቦና የሚመራ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት ከታችኛው እርከን የሚሰጡ ሥልጠናዎች ወሳኝ መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ በአሁኑ ወቅት ከ3 ሺህ በላይ ታዳጊዎች ልዩ ሥልጠና እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
የዚህ ሥልጠና ውጤታማነት በተግባር መታየት መጀመሩን ሲያስረዱም፣ ለሲካፋ ውድድር ከተመረጡት 25 የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች መካከል 17ቱ ከአዲስ አበባ የወጡ ታዳጊዎች መሆናቸው ስኬቱን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ መሆኑን አብራርተዋል።
መንግሥት የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ከመገንባት ጎን ለጎን፣ በወጣቶች ዘንድ ሥርዓትንና ዲሲፕሊንን የተከተለ ሥልጠና እንዲስፋፋ በትኩረት መሥራቱን እንደሚቀጥል ከንቲባዋ አረጋግጠዋል።
በበረከት ጌታቸው