ልጆች፤ እንዴት ናችሁ? በየሳምንቱ ወደ እናንተ የምናደርሳቸውን መረጃዎች በማንበብ እውቀት እየጨበጣችሁ እንደሆነ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የዛሬው ጽሑፋችን ደግሞ ከማንበብ ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ልጆች፤ ከመማሪያ መጽሐፎቻችሁ ውጭ ያሉ ሌሎች መጽሐፍትን ማንበብ ላይ እንዴት ናችሁ? ካነበባችሁስ ምን ጥቅም አገኛችሁባቸው? የሚለው ላይ ሐሳብ እንድትለዋወጡ እየጠየቅን ያነጋገርናቸው ልጆች በዚህ ላይ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡
ሶስና አወል እባላለሁ፡፡ የትምህርት ቤት መጽሐፍትን የጊዜ ሰሌዳ አውጥቼ አነባለሁ፡፡ ከእነዚህ መጽሐፍት ውጭ ደግሞ የተረት መጽሐፍትንም ከጓደኞቼ በመዋስ እና ከቤተ መጽሐፍት በመውሰድ አነባለሁ፡፡ የማነበውም ክፍል ውስጥ ብቻዬን ስሆን እንዲሁም የቤት ሥራ እና ጥናት ከጨረስኩ በኋላ ነው፡፡
እንደነዚህ ዓይነት መጽሐፍትን በማንበቤ ደግነትን እና ከጓደኞቼ ጋር እንዴት መግባባት እንዳለብኝ አስተምሮኛል፡፡ ከዚህ በፊት ለእኔ የተመቸኝን ብቻ ነበር ማድረግ የምፈልገው፡፡ መጽሐፉን ካነበብኩ በኋላ ግን የጓደኛዬን ስሜት መረዳት ጀመርኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ጥሩ ጓደኝነት እንዲኖረን አድርጎኛል፡፡
ዮርዳኖስ ዘሪሁን እባላለሁ። ትርፍ ጊዜዬን ከመጫወት ይልቅ አስተማሪና አዝናኝ መጽሐፍትን ማንበብ ያስደስተኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተረት መጽሐፍት፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ መዝገበ ቃላት አነባለሁ፡፡ መዝገበ ቃላት ማንበቤ የቃላትን ፍች እንዳውቅ ስላደረገኝ ከሰዎች ጋር በቀላሉ እንድግባባ አድርጎኛል፡፡
ቴዎድሮስ ዘሪሁን እባላለሁ፡፡ በትምህርት ቤትም ይሁን ቤት ውስጥ ማንበብ እወዳለሁ፡፡ በተለየ ሁኔታ ደግሞ የሚያዝናኑና የተረት መጽሐፍት ማንበብ ያስደስተኛል፡፡ ለትምህርቴ የሚረዱኝን መጽሐፍትም እንዲሁ፡፡
ተጨማሪ መጽሐፍት ማንበቤ አእምሮዬ እንዲፍታታ እና እውቀት እንዳገኝ አድርጎኛል፡፡ የማላውቃቸውን ነገሮች እንዳውቅ እና የንባብ ፍጥነቴ እንዲጨምር አግዞኛል፡፡
የሚያነቡ ልጆች ያሉትን አንብባችሁ ከእነሱ ልምድ እንደወሰዳችሁ እምነታችን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የባለሙያ አስተያየት አካትተናል፡፡
እምነቴ ድልነሳሁ እባላለሁ፡፡ የሕፃናት መጽሐፍት ደራሲ ነኝ፡፡ ልጆች ሁልጊዜ ክረምትና በጋ ሳትሉ በትርፍ ጊዜያችሁ መጽሐፍት ማንበብ አለባችሁ፡፡ የንባብ ልምድ ወይም ፍቅር ሲኖራችሁ የትምህርት መጽሐፍትንና ደብተራችሁን ለማንበብ ቀላል ይሆንላችኋል፡፡ ትምህርታችሁ ላይ ጎበዝ ትሆናላችሁ፡፡
ልጆች ማንበብ የማታውቁትን ነገር የምታውቁበት፣ ሕይወታችሁን የተሻለ የምታደርጉበት፣ ያላያችሁትን የምታዩበት፣ የጽሑፍ ችሎታችሁን የምታሻሽሉበት፣ የቃላትን ፍች የምታውቁበት ነው፡፡ ስለዚህ ምግብ ሳትመገቡ፣ ውኃ ሳትጠጡ እንደማትውሉት ሁሉ በየቀኑ አንድ ገጽ ማንበብ ይኖርባችኋል፡፡ ይህን ስታደርጉ አእምሯችሁን መገባችሁት ማለት ነው፡፡ ትርፍ ጊዜ ሲኖራችሁ ከቤተ መጽሐፍት እንዲሁም ቤተሰቦቻችሁ የሚገዙላችሁን መጽሐፍት አንብቡ፡፡ ስታነቡ ወደፊት መሆን የምትፈልጉትን ትሆናላችሁ፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ