የክብር መንደር፡ አዲስ አበባ የዜጎቿን ህይወት በተግባር የምትቀይርበት ታላቅ የትራንስፎርሜሽን ማሳያ

You are currently viewing የክብር መንደር፡ አዲስ አበባ የዜጎቿን ህይወት በተግባር የምትቀይርበት ታላቅ የትራንስፎርሜሽን ማሳያ

AMN- ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናችንን ለኑሮ ምቹ፣ ውብ እና የዜጎችን ሰብአዊ ክብር በላቀ ደረጃ የምትመጥን ስማርት ከተማ ለማድረግ የጀመረው ጉዞ እጅግ አስደናቂ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

በተለይም በክረምት በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር፣ ከተማዋን ለዘመናት ሲፈትኗት የነበሩ፣ የተጎሳቆሉ እና ለሰው ልጅ አኗኗር ፈጽሞ የማይመቹ አካባቢዎችን (እንደ ገዳም ሰፈር እና ጣልያን ሰፈር ያሉትን) ወደ ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮች ለመቀየር የተያዘው ራዕይ፣ የከተማዋን ሁለንተናዊ ዳግም ልደት በተግባር እያሳየ ይገኛል።

ግንባታው በክብርት ከንቲባ አማካኝነት በይፋ የተጀመረው “የአራዳ የበጎነት መንደር” የዚህ ታላቅ ራዕይ አንጸባራቂ ማሳያ ነው።

በዚህ ማራኪ ስፍራ የሚገነቡት ስምንት ባለ 9 ወለል የመኖሪያ እና ሁለት ባለ 4 ወለል የገበያ ማዕከል ህንፃዎች ፣ የኮንክሪት ክምችት ብቻ ሳይሆኑ፤ የነዋሪውን የተሻለ አኗኗር የሚያረጋግጡ ዘመናዊ የጋራ መገልገያዎች ፣ የተንጣለሉ አረንጓዴ ስፍራዎች እና ህፃናት በነፃነት ቦርቀው የሚያድጉባቸው የስፖርት ሜዳዎችን ያካተቱ ናቸው።

ከተማ አስተዳደሩ ዘንድሮ በክረምት በጎ ፈቃድ 2 ሺህ 500 ቤቶችን ለመገንባት አቅዶ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፤ ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ወደ እነዚህ ዘመናዊ ቤቶች ተመልሰው ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የዚህ ዜጋ ተኮር ስራ ሌላው እጅግ አስደናቂ ገጽታ፤ የተቋማት፣ የባለሀብቶች እና የመንግስት የላቀ ቅንጅት የታከለበት መሆኑ ነው።

የከተማዋ ባለሀብቶች የህዝብን አኗኗር ለመቀየር ለቀረበላቸው ጥሪ ቀና እና ፈጣን ምላሽ በመስጠት፤ በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች እያንዳንዳቸው ግዙፍ ህንፃዎችን በጋራ ለመገንባት ቃል ገብተው ወደ ስራ ገብተዋል።

ይህ ትብብር ከመሰረተ ልማት ግንባታ ባለፈ መተማመንን፣ አብሮነትን፣ ፅናትን እና ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትን በተግባር የሚያሳይ የብልፅግና መንገድ ነው።

በአጠቃላይ የአዲስ አበባ የክረምት በጎ ፈቃድ ስራ በቤት ግንባታ ብቻ የተገደበ አይደለም።

አካባቢን ማጽዳት፣ የጎርፍ መከላከያዎችን መገንባት፣ አቅመ ደካሞችን ማዕድ ማጋራት፣ ደም መለገስ፣ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ መትከል፣ የማጠናከሪያ ትምህርት እና ነፃ የህክምና አገልግሎት መስጠትን ያካተተ እጅግ ሰፊ ሀገራዊ የፍቅር ንቅናቄ ነው።

አዲስ አበባ የዜጎቿን እንባ የምታብስ፣ ውበቷ ከሰብአዊነት ጋር የተዋሃደ፣ እና በተግባር የነዋሪዎቿን ህይወት ትራንስፎርም የምታደርግ ከተማ መሆኗን በጉልህ እያረጋገጠ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review