AMN ጥር 23/2018
የኢትዮጵያ የልማት ስኬቶች ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥኑ መሆናቸውን የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ፣ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በተገኙበት ሸበሌ ሪዞርትን መርቀዋል።
በዚሁ ጊዜ የጂቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ፤ የሸበሌ ሪዞርት ድንቅ ቀጣናዊ የቱሪዝም ትስስርን የሚያጠናክር የልማት ውጤት ነው ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት በቱሪዝምና ሌሎች የልማት መስኮች የተገኙ ውጤቶች ቀጣናዊ የዕድገት ትስስርን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሸበሌ ሪዞርትም ቀጣናዊ የቱሪዝም ልማትን የሚያሳድግ አስደማሚ የመስህብ መዳረሻ የልማት ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱም የኢኮኖሚ ትስስርን የበለጠ በማጎልበት ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
የሶማሌ ክልል ህዝብም ሰላሙን በማስጠበቅ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ውጤቶች እንዲገኙ ያበረከተው አስተዋጽኦ የሚደነቅ መሆኑን አብራርተዋል።
በቀጣይም በሀገር ውስጥና በውጭ ዓለማት የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ኢትዮጵያንና የቀጣናውን ሀገራት ህዝብ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረጉ ጥረቶች የድርሻቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።