ለተማሪዎች ውጤት እና ስነ-ምግባር መሻሻል የመምህራን እና የወላጆች ክትትል ወሳኝ ነው

You are currently viewing ለተማሪዎች ውጤት እና ስነ-ምግባር መሻሻል የመምህራን እና የወላጆች ክትትል ወሳኝ ነው

AMN – ጥር 25/2018 ዓ.ም

ለተማሪዎች ውጤት እና ስነ-ምግባር መሻሻል የመምህራን ብቃት እና የወላጅ ክትትል ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ለተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባር መሻሻል ወሳኝ ሚና የሚጫወተው “የመምህራን የማስተማር ብቃት ነው ወይስ የወላጅ ክትትል ነው?” በሚል ርዕስ ሙያዊ ክርክር ተካዷል፡፡

መያዊ ክርክሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ዘወትር ሰኞ ማለዳ የሚያካሂደው የዕውቀት ሽግግር መርሀ ግብር አካል ሲሆን በየሩብ አመቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የሚካሄድ ነው፡፡

በዛሬው ዕለት በተካሄደው መድረክም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የመጡ ምሁራንን ጨምሮ የትምህርት ማህበረሰብ አባላት በተገኙበት የተካሄደ ነው ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ለተማሪዎች ውጤት እና ስነ-ምግባር መሻሻል የመምህራን የማስተማር ብቃት እና የወላጅ ክትትል ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ቤት ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ በርካታ ተጸዕኖዎች ውስጥ እንደሚያልፉ የጠቆሙት ኃላፊው ተማሪዎቹ ለዚህ ተጸዕኖ እንዳይጋለጡ ወላጆች፣መምህራን፣ርዕሰ መምህራን እና ሌሎች የትምህርቱ ማህበረሰብ ሊወጣው የሚገባ ኃላፊነት መኖሩን አጸንዖት ሰጥተዋል፡፡

ትውልድ የሚታነጸው በጋራ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ይህንን የጋራ እንቅስቃሴ ማምጣት የሚችለው ደግሞ የትምህርት አመራሩ ነውም ብለዋል፡፡

የወላጅ እና መምህር ሚናን በማቀናጀት ለተሻለ ውጤታማነት መትጋት ይገባልም ሲሉ ሃላፊው ተናግረዋል ፡፡

በሃብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review