AMN ጥር 29 ቀን 2018 ዓ.ም
ለዝውውር በርካታ ገንዘብ የሚወጣባቸው ተጫዋቾች ከሌሎች በበለጠ አእምሮአዊ ጥንካሬ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይነገራል፡፡ የዝውውር ገንዘቡ ከፍ ሲል የተለየ አብርክቶ እንዲኖራቸው ይጠበቃል ፤ ይህን ካላደረጉ ጫናው ፈታኝ ይሆንባቸዋል።
በተለይ አሁን የማህበራዊ ሚዲያ በተስፋፋበት ዘመን ከየአቅጣጫው የሚወረወረው ትችት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ለመተው ጠንካራ አእምሮአዊ ጥንካሬ ያስፈልጋል፡፡ ይህን መቋቋም ተስኗቸው ከመንገድ የቀሩ በርካታ ተጫዋቾች አሉ፡፡ ሊቨርፑል 116 ሚሊየን ፓውንድ ለመክፈል ተስማምቶ አንፊልድ ያደረሰው ፍሎሪያን ቨርትዝ የዚህ እጣ እንዳይደርሰው ያሰጋ ነበር፡፡
የ22 ዓመቱ ጀርመናዊ አሌክሳንደር ኢዛክ እስኪ መጣ የእንግሊዝ ውዱ ተጫዋች ሆኖ አንፊልድ መድረሱ ከእርሱ ብዙ እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡ ፍሎሪያን ቨርትዝ ግን በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት የሰላ ትችት ሲገጥመው ነበር፡፡ አብዝቶ አካላዊ ጥንካሬ ለሚፈልገው የእንግሊዝ እግርኳስ አይሆንም የሚሉ ድምፆች ጎልተው ተሰምተዋል፡፡
አሁን ግን ተጫዋቹ በጀርመን ባየር ሊቨርኩሰን እያለ ያሳየውን አስደናቂ ብቃት በእንግሊዝም ማሳየት እንደሚችል ፍንጭ እያሳየ መጥቷል፡፡ በተለይ ሊቨርፑል ኒውካስትል ዩናይትድን በአንፊልድ 4ለ1 ሲረታ በነበረው ተፅእኖ ሙገሳ ጎርፎለታል፡፡
ቨርትዝ የእንግሊዝ እግርኳስ የሚፈልገውን አካላዊ ጥንካሬ ለማምጣት ብዙ እየለፋ ይገኛል፡፡ አሁን ላይ የዚህ ጠንካራ ስራው ውጤቱን መመልከት ጀምሯል፡፡ ከቡድን አጋሮቹ ጋር የበለጠ መግባባት ችሏል፡፡ ከሁጎ ኢኪቲኬ ጋር የፈጠረው ጥምረት የሊቨርፑል ደጋፊዎች መጪው ዘመን ብሩህ እንደሚሆን በድፍረት እንዲናገሩ እያስቻላቸው ነው፡፡ ሁለቱ ተጫዋቾች በጥምረታቸው በሁሉም ውድድር ስድስት ግቦችን አስገኝተዋል። በፕሪምየር ሊጉ በሁለት ተጫዋቾች ጥምረት ይህን ያህል ግብ ያገኘ ክለብ የለም፡፡
ቨርትዝ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ “ኢኪቲኬ ድንቅ ተጫዋች ነው ፤ በጀርመን እያለሁ እርሱን በተቃራኒ ገጥሜዋለሁ ፤ ሊቨርፑልን ከተቀላቀልኩ በኋላ ገና በልምምድ ባየሁት ነገር ተደንቄያለሁ ፤ በዚህ ደረጃ ምርጥ ተጫዋች መሆኑን አልተረዳሁም ነበር ፤ ከእርሱ ጋር መጫወት በጣም አስደሳች ነው ፤ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ የመረዳት አቅሙ ከፍ ያለ ነው፡፡ ” በማለት ስለ ፈረንሳዊው አጥቂ ተናግሯል፡፡
ፍሎሪያን ቨርትዝ ከሁጎ ኢኪቲኬ ጋር የፈጠረው ጥምረት ብቻ ሳይሆን በብዙ መንገድ ተሸሽሏል፡፡ አሰልጣኙ አርነስሎት በመጀመሪያዎቹ ወራት እንደነበረው እርሱን ለማሰለፍ አያመነቱም፡፡ የቡድን አጋሮቹም በተጫዋቹ ላይ ያላቸው እምነት ጨምሯል፡፡ እርሱም በራስ መተማመኑን አሳድጓል ፤ ሊቨርፑል 116 ሚሊየን ፓውንድ ለመክፈል ተስማምቶ ለምን እንዳመጣው እያሳየ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ ፍሎሪያን ቨርትዝ እራሱን መስሏል፡፡ የሊቨርፑል ደጋፊዎችም ተጫዋቹን በስስት ማየት ጀምረዋል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ