የአዲስ አበባ ፖሊስ የሥነ-ምግባር ጉድለት ያለባቸው 104 አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ፖሊስ የሥነ-ምግባር ጉድለት ያለባቸው 104 አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱን ገለጸ

AMN – ጥር 29/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፥ ተቋሙን በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ለማዘመን እየተከናወነ ባለው የሪፎርም ሥራ፣ ከፖሊስ አገልግሎት ተቃራኒ የሆኑ ተግባራትን በፈጸሙ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ ይህን የተናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው።

ኮሚሽነሩ በምላሻቸውም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በሥነ-ምግባር ብልሽት እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ 104 የፖሊስ አባላት ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጉን ገልጸዋል።

እርምጃው የተወሰደው በተደጋጋሚ ትምህርት ተሰጥቷቸው ሊታረሙ ባልቻሉና ሕዝብን በታማኝነት ማገልገል ባልቻሉ አባላት ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

ከተሽከርካሪ ታርጋ መፍታት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት ኮሚሽነር ጌቱ፥ ይህንን አሠራር በዘላቂነት ለማስቀረት የታርጋ ለውጥ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ አዲስ የታርጋ ለውጥና የቁጥጥር ሥራ መጀመሩን በመጥቀስ ከዚህ በኋላ ታርጋ በመፍታት ሒደት የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደሚቀሩና በዘመናዊ የቴክኖሎጂ ቁጥጥር እንደሚተኩ አስረድተዋል።

ከሕገ-ወጥ ስደተኞች ቁጥጥር ጋር በተያያዘም፣ ከኢሚግሬሽን፣ ከፌደራል ፖሊስና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ ፖሊስን አዲስ አበባን የሚመጥን፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈና በሕዝብ አመኔታን ያተረፈ ተቋም ለማድረግ የሚከናወነው የሪፎርም ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በሚካኤል ኅሩይ እና በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review