AMN የካቲት 01 ቀን 2018 ዓ.ም
ሊቨርፑል ከማንችስተር ሲቲ ባለፉት አስር ዓመታት የነበራቸው ግንኙነት ዋንጫውን ማን ያሸንፋል የሚለውን ለመመለስ ፍንጭ የሚሰጥ ነበር።
የርገን ክሎፕ እና ፔፕ ጋርዲዮላ ሊጉ መቼም የማይዘነጋው ከፍያለ ፉክክር አሳይተዋል። ሁለቱ ክለቦች የመጨረሻዎቹ ስምንት የሊግ ዋንጫዎችን ተቋድሰዋል። ማንችስተር ሲቲ ስድስቱን ሲወስድ ሊቨርፑል ሁለቱን ወደ ካዝናው ከቷል።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ግን ዋንጫው ከሁለቱ ውጪ የመሆን እድል የሰፋ ይመስላል። ያለፉትን ሦስት የውድድር ዓመት ድል ያጣጣሙ ቡድኖችን ሲከተል የቆየው አርሰናል ተከታይነቱ አብቅቶ ቀዳሚ ለመሆን መንገዶች አልጋ በአልጋ ሆነውለታል።
ሊቨርፑል እና ማንችስተር ሲቲ በሂሳባዊ ስሌት ከዋንጫ ፉክክር ባይርቁም አርሰናልን የሚያስጨንቅ ብቃት ግን እያሳዩ አይደለም። በተለይ መድፈኞቹን በቅርብ እርቀት የሚከተለው ማንችስተር ሲቲ ከመጨረሻዎቹ ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ዎልቭስን ብቻ ነው። በ24ኛ ሳምንት ቶተንሃምን 2ለዐ እየመራ አቻ መውጣቱ ማንችስተር ሲቲ ላይ እምነት የነበራቸውን ሰዎት ተስፋ ያስቆረጠ ነበር።
ከዋንጫ ይልቅ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ለማግኘት የሚጠረው ሊቨርፑልም ቢሆን ከመጨረሻዎቹ ስድስት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ነው ያስመዘገበው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች ዛሬ ምሽት 1:30 በአንፊልድ ይፋለማሉ።
ማንችስተር ሲቲ በኢትሃድ የተደረገውን የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ 3ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል። ሲቲ ከዋንጫው ፉክክር ላለመራቅ የመጀመሪያ ዙር ድሉን መድገም ይጠበቅበታል።
ከመሪው አርሰናል በ14 ነጥብ የሚርቀው ሊቨርፑል ጨዋታዎችን ማሸነፍ ካልቻለ ቻምፒየንስ ሊግ የመሳተፍ እድሉም አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ ይችላል። የማንችስተር ዩናይትድ እና ቼልሲ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ለሊቨርፑል ስጋት ሆኗል።
በዛሬው ጨዋታ በሊቨርፑል በኩል ጥሩ ጥምረት እየመሰረቱ የሚገኙት ፍሎሪያን ቨርትዝ እና ሁጎ ኢኪቲኬ ይጠበቃሉ። በሲቲ በኩል አንቷን ሴሜንዮ እና ራያን ቸርኪ ልዩነት ፈጣሪ ሊሆኑ ይችላሉ።
በጨዋታው በሊቨርፑል በኩል አዲስ የጉዳት ዜና የለም። አርነ ስሎት ሁለቱንም የቀኝ መስመር ተከላካዮች ኮኖር ብራድሊ እና ጀርሚ ፍሪምፖንግ ቀድሞ በጉዳት በማጣቱ ዶሚኒክ ሶቦስላይ ቦታውን ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል።
ማንችስተር ሲቲ ተከላካዩ ጆን ስቶንስ ወደ ልምምድ ቢመለስለትም ለዛሬ ጨዋታ ይደርሳል ተብሎ አይጠበቅም። ጀርሚ ዶኩ እና በርናንዶ ሲልቫም መግባታቸው አልተረጋገጠም።
ሊቨርፑል በአንፊልድ ማንችስተር ሲቲ ላይ ያለው የበላይነት ከፍ ያለ ነው። የመርሲሳይዱ ክለብ በሜዳው ማንችስተር ሲቲን ባስተናገደባቸው የመጨረሻ 22 ጨዋታዎች የተሸነፈው በአንዱ ብቻ እንደሆነ የኦፕታ ቁጥራዊ መረጃ ያሳያል።
ማንችስተር ሲቲ በአንድ የውድድር ዓመት በሊጉ ሊቨርፑልን በደርሶ መልስ ካሸነፈ 88 ዓመታት ተቆጥረዋል። በአንፊልድ በዚህ ልክ የሚቸገረው የፔፕ ጋርዲዮላው ቡድን ከዋንጫ ፉክክሩ ላለመራቅ ታሪክ መቀየር ይኖርበታል።
ምሽት 1:30 የሚጀምረውን ጨዋታ ክሬግ ፓውሰን በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ 11 ሰዓት ላይ ብራይተን በአሜክስ ስታዲየም ክሪስታል ፓላስን ያስተናግዳል።
በሸዋንግዛው ግርማ