የባህር በር ጥያቄያችን የህልውና እንጂ የቅንጦት አይደለም – ምሁራን

You are currently viewing የባህር በር ጥያቄያችን የህልውና እንጂ የቅንጦት አይደለም – ምሁራን

AMN- የካቲት 3/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ እያሳየች ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል እና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆና ለመቀጠል የባህር በር ባለቤትነት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ምሁራን ገልጸዋል።

እንደ ምሁራኑ ገለጻ፣ የባህር በር ማግኘት ከኢኮኖሚ ባለፈ ሀገረ መንግስትን የማጽናት እና ሉአላዊነትን የማስከበር የህልውና ጉዳይ ነው።

የህዝብ አስተዳደርና ፖሊሲ ባለሙያው ገመቹ አራርሳ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ገናና እና የባህር በር ባለቤት የነበረች ሀገር ናት።

በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መሆኑን ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር እየመሰከሩ ይገኛሉ።

የባህር በር ካለህ ገበያህ መላው ዓለም ነው፣ የባህር በር ከሌለህ ደግሞ ገበያህ የጎረቤት ሀገራት ብቻ ይሆናል የሚሉት ዶክተር ገመቹ፣ የባህር በር ፍላጎት ተፈጥሯዊና የኢኮኖሚ እድገት የሚጠይቀው ግዴታ መሆኑን ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላምና የኢኮኖሚ ትስስርም ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

ጥያቄው በታሪክ፣ በህግ እና በኢኮኖሚ እይታ ተገቢ ነው ያሉት ባለሙያው፣ የባህር በር ማግኘት ለሁሉም የሚጠቅም እንጂ የትኛውንም ሀገር የሚጎዳ አለመሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አብራርተዋል።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የባህር በር ጥያቄ የፍትሀዊነት እንጂ የቅንጦት አለመሆኑን ያነሳሉ።የባህር በር ባለቤትነት ከብሔራዊ ደህንነት እና ከመከላከያ አቅም ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዳለውም ይገልጻሉ።

ሀገርን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ግብአቶች በባህር ነው የሚመጡት የሚሉት ዶክተር ብርሃነ መስቀል፣ የባህር በር በሌላ አካል ቁጥጥር ስር መሆኑ ሉአላዊነትን ለማስከበር ትልቅ ፈተና እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያን ከባህር በር የመግፋት ጉዳይ በታሪካዊ ጠላቶች የታቀደ ደባ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ማረም ለሚቀጥለው ትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ኃላፊነት መሆኑንም አሳስበዋል።

በርካታ የውጭ ሀገራት በታላቅ ፉክክር የጦር ሰፈራቸውን በሚመሰርቱበት ቀጣና፣ የአካባቢው ሀገራት በኢኮኖሚ ተሳስረው ሉአላዊነታቸውን ሊያስከብሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የራሷን ኢኮኖሚ በባለቤትነት ለመምራት እና ሉአላዊነቷን ለማጽናት የምታደርገው ጥረት በመሆኑ፣ ጎረቤት ሀገራትም በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ ምሁራኑ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review