AMN – የካቲት 2/2018 ዓ.ም.
ሁሉን አቀፍ ዕድገትን ለማረጋገጥ፣ የማኅበረሰብን የመቋቋም አቅም ለመገንባትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ማረጋገጣቸውን የኢትዮጵያ መንግሥትና የልማት አጋሮች ቡድን (DPG) በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ዛሬ በአዲስ አበባ በተካሄደው ከፍተኛ የልማት ፎረም (HLDF) ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የልማት ድርጅቶችና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
ፎረሙ በዋናነት ሁሉን አቀፍ በሆነ ዘላቂ ልማት እንዲሁም በአገራዊ ምክክርና ሰላም ግንባታ ሒደት ላይ ትኩረት አድርጎ መክሯል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ባስተላለፉት መልዕክት “ኢትዮጵያ የተጀመረውን የሪፎርም አጀንዳ ሙሉ በሙሉ በመተግበር ለዘላቂ ሰላምና ለሁሉን አቀፍ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ትቀጥላለች” ብለዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ የሰባት በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡንና ይህም በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፎች በተመዘገቡ ውጤቶች መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጸዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የ9.2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧንና በያዝነው ዓመት ደግሞ ዕድገቱ ወደ 10.2 በመቶ ከፍ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ ኢድሪስም ሀገራዊ ምክክሩ የሀገሪቱ የሕልውና ጉዳይ መሆኑንና በንግግር፣ ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም ሥራ (DDR) እና በሽግግር ፍትሕ ላይ የተመሠረተ የሰላም አጀንዳ እየተተገበረ መሆኑን አብራርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2027 ለምታስተናግደው የዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባዔ (COP32) ዝግጅት እያደረገች መሆኑንና ይህም ለአፍሪካ የአረንጓዴ ልማት አጀንዳ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የልማት አጋሮች ድጋፋቸው ሀገሪቱ ቅድሚያ ከምትሰጣቸው ጉዳዮች ጋር የተጣጣመና ግልጽነት የተሞላበት እንዲሆን ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
መንግሥትም ዓለም አቀፍ አጋሮች ለሀገሪቱ የሪፎርም ጉዞ የሚሰጡት ድጋፍ ሊተነበይ የሚችልና በውጤት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል።