AMN- የካቲት 6/2018 ዓ.ም
ማቲ እቅድ እ.አ.አ በ1950ዎቹ ጣሊያን የሰሜን አፍሪካ ሀገሮች ኢኮኖሚያቸውን እና የተፈጥሮ ሃብታቸውን ያበለጽጉ ዘንድ በጣሊያናዊው የህዝብ አስተዳደር ባለሙያ፣ የንግድ ሰው፣ የፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለሙያና የሀገሪቱ የነዳጅሃብት ባለስልጣን በነበሩት ኢንሪኮ ማቲ የተዋወቀ እንደሆነ ይገለፃል፡፡
እቅዱ የጣሊያን – አፍሪካ ትብብርን የሚያፋጥንና ግንኙነታቸውን ለማደስ እንደሚያስችል እምነት ተጥሎበታል።
በአሁኑ ወቅት የማቲ እቅድ በ14 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ እየተተገበረ ሲሆን ቁጥሩንም ለመጨመር እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።
ጣሊያን ከተመረጡ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ለአራት አመታት ለመተግበር ያቀደችው ሁለቱንም ወገን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ለተባሉ ፕሮጀክቶች የሚተገበረው ማቲ እቅድ በአመት 3 ቢሊየን ዩሮ የሚያወጣ ነው።
ለመነሻ ያህልም ጣሊያን 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ዩሮ ፈንድ የምታደርግ መሆኑንና ከዚህ ውስጥ ለሀይል አቅርቦት፣ ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለጤናና ለትምህርት ዘርፎች ፕሮጀክቶች በብድር መልክ እንደሚሰጥ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሚሎኒ ባለፈው አመት ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በመከሩበት ወቅት አስታውቀዋል።
የትኛውም የወደፊት የተባበረና የልማት ሞዴል ያለ አፍሪካ ማሰብ አይቻልም የሚሉት ሚኒስትሯ የማቲ እቅድ አህጉሪቱን እንደ ችግር ሳይሆን እንደ እድል የምናይበት፣ ከላይ ወደ ታች ትዕዛዝ የምንሰጥበት ሳይሆን በክብር የምንመለከትበት አዲስ መንገድ ነው ብለዋል።

የሀይል አቅርቦት ትብብር ላይ የሚያተኩረውና ከዚህ ጎን ለጎን ጤና፣ ትምህርትና ሌሎች ዘርፎችንም የሚነካው እቅዱ ዋና አላማውን ከአፍሪካ ለሚነሳውና በርካቶች በገፍ ለሚያደርጉት ስደት መሰረታዊ ምክንያት የሆነውን የኢኮኖሚ ችግር ማቃለል አድርጓል።
የጣሊያን መፃኢ እድል በአፍሪካ አህጉር የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የሚናገሩት ሚኒስትሯ አህጉሪቱ ካሏት ግዙፍ ተፈጥሮአዊ ሃብቶች በመነሳት እንድታድግና እንድትበለጽግ የሚያግዝ የጣሊያን ስትራቴጂካዊ ፕሮጀክትና የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል፡፡
ጣሊያን ከአፍሪካ ጋር የነበራትን ታሪካዊ ግንኙነት በተሻለና ዘመኑን በዋጀ ደረጃ ለማጠናከር ይዛ የመጣችው እቅድ በበርካታ አፍሪካውያን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ነው። አህጉሪቱ ከያዘቻቸው ረዥምና አጭር እቅዶች ጋርም የተጣጣመ መሆን ችሏል።
እንዲሁም ጣሊያን በማቲ እቅድ ስልታዊ አጋር ካደረገቻቸው የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን በማቴ እቅድ ውስጥ ኢትዮጵያ ተመራጭና ተጠቃሚ መሆኗ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ስልታዊ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል። ይህም የኢኮኖሚና የልማት ትብብር ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል።
ሁለተኛው የጣሊያን-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ሲካሄድ ይህን ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባዔ እንድታስተናግድ አዲስ አበባ ተመርጣለች።
በትዝታ መንግስቱ