ኢትዮጵያ ዳግም የዲፕሎማሲ መናኸሪያነቷን ማረጋገጥ ችላለች – የመንግስት ኮሙኑኬሽን አገልግሎት

You are currently viewing ኢትዮጵያ ዳግም የዲፕሎማሲ መናኸሪያነቷን ማረጋገጥ ችላለች – የመንግስት ኮሙኑኬሽን አገልግሎት

AMN – የካቲት 7/2018 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባዔ እና በዛሬው ዕለት የተጀመረው 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በስኬት መካሔዱን የመንግስት ኮሙኑኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ምድር ሲካሄድ የመጀመሪያው የሆነው የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባዔ ዋና ዓላማው በአፍሪካ እና በጣሊያን መካከል ያለውን የቆየ ትብብር ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማሳደግ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው በመግለጫቸው ተናግረዋል።

የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አፍሪካ ያላት ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ ወጣትና የተማረ የሰው ኃይል በቀጣዩ ዓለም ላይ የተሻለ ዕድል እንዲኖራት የሚያደርጋት መሆኑም በጉባዔው ላይ ስለመናገራቸው ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

ጣሊያን ከፍሪካ ጋር በጤና፥ በትምህርት፥ በኃይል አጠቃቀም፥ በግብርና እና በውሃ ላይ በትብብር መሥራት ስለምትችልባቸው መንገዶች አንስተው ውይይት ስለመደገረጉም አንስተዋል።

በሌላ በኩል “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽሕና አጠባበቅ ሥርዓት ለአጀንዳ 2063” በሚል መሪ ሀሳብ መካሔድ በጀመረው የሕብረቱ የመክፈቻ ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ካላት የውሃ ሀብት አጠቃቀም አንጻር የታላቁ የሕዳሴ ግድብን ስኬትና የፍትሐዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄዋን ጨምሮ ሌሎች አንገብጋቢ የውሃ ጉዳዮችን ማንሳታቸውንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒትስሩ ኢትዮጵያ በአምስቱ የኢኮኖሚ መስኮች እያከናወነች ስላለው ተግባር ለተሳታፊዎቹ ማብራራታቸውን ያስታወቁት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም በግብርናው ዘርፍ በስንዴ ራስን ለመቻል እና በዲጂታል ኢኮኖሚው ዘርፍ በ”ሞሰብ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ያስመዘገበችወ ውጤት ለአፍሪካውያን ሀገራት ተምሳሌት መሆኑን ያነሱ ሲሆን ሀገራችን ስለጀመረችው አዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ በሰጡት ገለጻ ሁሉም ተሳታፊዎች አድናቆታቸውን ስለመግለጻቸው አስታውቀዋል።

በዚህ ታሪካዊ ጉባዔ ላይ በድምሩ 26 ነገስታት፣ ርዕሳነ ብሔራት፣ የሀገር መሪዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተገኙ ሲሆን ኢትዮጵያም በመደበኛው ጉባዔ ካቀረበችው ሀሳብ ባሻገር፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ጨምሮ ከተለያዩ መሪዎች ጋር ውጤታማ የሆነ ሁለትዮሽና የጎንዮሽ ውይይቶችን አድርጋለች ብለዋል።

እነዚህ ጉባዔዎች ኢትዮጵያ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የማስተናገድ ብቃቷ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንና አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መቀመጫነቷን በድጋሚ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን የመንግስት ኮሙኑኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review