የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎማለፍ ጨዋታዎች

You are currently viewing የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎማለፍ ጨዋታዎች

AMN የካቲት 10 ቀን 2018 ዓ.ም

በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ በሊግ ምዕራፍ ውድድራቸው ከ9 እስከ 24ኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ክለቦች የጥሎማለፍ ጨዋተቸውን ዛሬ ይጀምራሉ፡፡

በደርሶ መልስ በሚደረጉት በእነዚህ ጨዋታዎች አሸናፊ የሚሆኑ ስምንት ክለቦች በቀጥታ ካለፉ ስምንት ክለቦች ጋር ይፋለማሉ፡፡

ዛሬ አራት ጨዋታዎች ሲከናወኑ ቤኔፊካ ከሪያል ማድሪድ በስታዲዮ ዳሉዝ ምሽት 5 ሰዓት የሚያደርጉት ግጥሚያ ይጠበቃል፡፡ ሁለቱ ክለቦች በሊግ ምዕራፍ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ተገናኝተው በጆዜ ሞሪንሆ የሚመራው ቤኔፊካ 4ለ2 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

በድራማ በታጀበው እና ሪያል ማድሪድ ሁለት ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ ባጣበት ጨዋታ ቤኔፊካን ያሳለፈች ወሳኟን አራተኛ ግብ ግብ ጠባቂው አናቶሊ ትሩቢን ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡ ሽንፈቱ የስፔኑ ክለብ በቀጥታ ስምንት ውስጥ ገብቶ እንዳያልፍ ትልቅ መሰናክል ሆኖበታል፡፡

ዳግም የተገናኙት ሁለቱ ክለቦች የዛሬው ፍልሚያቸው የመልስ ጨዋታ እንደመኖሩ በበርካታ ግብ ይታጀባል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የቀድሞ ክለባቸውን የመግጠም ሌላ እድል ያገኙት ጆዜ ሞሪንሆ “ሪያል ማድሪድ የቆሰለ አንበሳ ስለሆነ አደገኛ ይሆናል” ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ቤኔፊካ ይበልጥ ጥንቃቄ የተሞላበት አቀራረብ ሊያሳይ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአልቫሮ አርቤሎአ የሚሰለጥነው ሪያል ማድሪድ በዛሬው ጨዋታ ኪሊያን ምፔን መልሶ ያገኛል፡፡ ፈረንሳዊው አጥቂ በላሊጋው ማድሪድ ሪያል ሶሲዬዳድን 4ለ1 ሲረታ በጉልበት ጉዳት በጨዋታው አልተሳተፈም፡፡

ሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ አራት ጊዜ ተገናኝተው ቤኔፊካ ሦስቱን በድል ተወጥቷል፡፡ ሪያል ማድሪድ የፖርቹጋሉን ክለብ ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች የባለፈው ውድድር ዓመት የቻምፒየንስ ሊጉ አሸናፊ ፓሪሰን ዠርማ ወደ ስታድ ሊውስ 2ኛ አቅንቶ ከሞናኮ ጋር ይጫወታል፡፡ ቦሩሲያ ዶርትመንድ በሜዳው ሲግናል ኤዱና ፓርክ አታላንታን የሚያስተናግድበታ ጨዋታም ይጠበቃል፡፡ ሁለቱም ጨዋታዎች ምሽት 5 ሰዓት ይጀምራሉ፡፡

ምሽት 2፡45 ላይ የቱርኪዬው ክለብ ጋላታሳራይ በሜዳው ራምስ ፓርክ ከጁቬንቱስ ጋር ይጫወታል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review