የኢትዮጵያና ቱርክዬ ትስስር ለቀጣናዊ ሰላምና ትብበር

You are currently viewing የኢትዮጵያና ቱርክዬ ትስስር ለቀጣናዊ ሰላምና ትብበር

AMN- የካቲት 10/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያና ቱርክዬ ግንኙነት ዘመናትን የተሻገረ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሁሉ በአጋርነት የቀጠለ ነው፡፡

ኢትዮጵያና ቱርክዬ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ ከዚያ ባሻገር ካላቸው ሚና አንፃር የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ቀጣናዊ እንድምታው ከፍ ያለ ነው፡፡ ቱርክዬ በአውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪካ ቀጣናዊ ዋና ተዋናይ ሆና ብቅ ካለች ሰነባብታለች፡፡

ቱርክዬ እ.ኤ.አ ከ1990ዎቹ ወዲህ፣ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ አፍሪካን በሚመለከት ትልቅ ለውጥ ማሳየቷን ነው አሰሲንግ ቱረክዬ -አፍሪካ ኢንጌጅመን በሚል ርዕስ መጽሐፍ ያሳተሙት ዲፓማና ፓርላር የጠቀሱት፡፡

እ.ኤ.አ 1998 አፍሪካ አክሽን ፕላን በመቅረጽ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በስትራቴጂ ዳግም ለማጽናት መንገድ ከፍታለች፡፡ በመቀጠልም ኦፕን ቱ አፍሪካ ፖሊሲ እ.ኤ.አ በ2005 ይፋ በማድረግ ግንኙነቷን አድሳለች፡፡ ቱርክዬ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በማሸማገል ዲፕሎማሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ መሆን እንደቻለች ይጠቀሳል፡፡

ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሊቢያ፣ አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ እስራኤል፣ አዘርባጃን፣ ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ፍልስጤም እና ኢራን በቱርክዬ የማሸማገል ዲፕሎማሲ ተጠቃሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በገጸ-ድሩ ባወጣው መጣጥፍ ገልጧል፡፡

ኢትዮጵያና ቱርክዬ ሁለቱም ትልቅ የማንሰራራት ምዕራፍ ላይ የሚገኙ መሆናቸው በጋራ ፍላጎትና በጋራ ጥቅም እንዲተሳሰሩ ያስችላቸዋል፡፡ የቱርክዬ የማሸማገል ዲፕሎማሲ ተቀባይነት ማሳያ ተደረገው ከሚጠቀሱት አንዱ በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ያካሄደችው ነው፡፡

የድርድሩ ውጤት ቱርክዬ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ትስስርን በመጠቀም የማሸመገል ዲፕሎማሲን ያሳካችበት መንገድ ለሌሎችም መካከለኛ ኃይሎች ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ይጠቀሳል፡፡

በዚህ ስምምነት ወቅት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሰላማዊ መሆኑንና ጎርቤት ሀገራትን የሚጠቅም በጥርጣሬ ሳይሆን በትብብር መንፈስ መታየት ያለበት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋንም የተደረሰውን ስምምነት በማድነቅ ኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነትን ተገቢነት ማግኘቷም አይቀሬ መሆኑን መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

ይህ የማስማማት ሚናዋ ቱርክዬ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም እንዲሰፍን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ነው የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ባወጣው መጣጥፍ የገለጸው፡፡

በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል መግባባት እንዲደረስ የቱርክዬ የማሸማገል ጥረት በስተመጨረሻም የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲያዊ መድረክ ህጋዊነትን ያላበሰ ሆኗል፡፡

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በህዳሴ ግድብ ላይ ጫና ለማሳደር ላይ ታች በሚሉበት ጊዜ፣ ቱርክዬ በገለልተኝነት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን እንድታስጠብቅ ያስቻለ አቋም መያዟ ተመራጭ ያደርጋታል፡፡

የአንካራ ስምምነት፣ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ስንጥቃት በመድፈን በአፍሪካ ቀንድ ያንዣበበውን የግጭት ደመና የገፈፈ መሆኑ፣ የኢትዮጵያና ቱርክዬ ግንኙነት በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ቁልፍ ሚና የሚኖረው ይሆናል፡፡

የቱርክዬ አቋም የማሸማገል ሚና፣ ኢትዮጵያ ግጭቶች እንዲፈቱ በሰላም ማስከበርና በማደራደር በጎረቤት ሀገራት ካላት አስተዋጽኦ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ፣ የሀገራቱ ግንኙነት በቀንዱም ሆነ በባህረ ሰላጤው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚኖረው ተጽዕኖ የጎላ ይሆናል፡፡

ቱርክዬ የኢትዮጵያን ሕጋዊ የባሕር በር ተደራሽነት ጥያቄ በመደገፍ እውን እንዲሆን አዎነታዊ ሚና እንደሚኖረው ነው የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት አጽንኦት የሰጠው፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ስራቴጂካዊ ስፍራ ያላት፣ የአውሮፓ፣ ኢስያ እና የመካከለኛው ምስራቅ መግቢያ በር ተደርጋ የምትወሰደው ኢትዮጵያ፣ አሁን ላይ የኃይል ሚዛን አስጠባቂ ሀገር፤ በአፍሪካ እና በአፍሪካ ሕብረት የሰላምና መረጋጋት ጋሻ ተደርጋም ትቆጠራለች፡፡

ኢትዮጵያ ያላት ጂኦፓለቲካዊ ስፍራ፣ የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ሚናዋ እና አዳጊ የኢኮኖሚ አቅሟ ቱርክዬ ወዳጅ አድርጋት እንድትቆይ ምክንያት ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅት ዓለም ፊቷን ባዞረበት ወቅት ከጎኗ የሆኑ ወዳጆችን እንደማትዘነጋ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በርግጥ ቱርክዬ ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ወሳኝ ወቅት ከጎኗ በመቆም ጥሩ ወዳጅነታቸውን ካሳዩ ጥቂት ወዳጆች መካከል አንዷ ናት፡፡

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review