AMN- የካቲት 12/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን ውብ ለማድረግ፣ አዲስ ገፅታ ለማላበስና አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና መርሐ ግብር አከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ አዲስ አበባ ከተማ በሰላማዊነቷ፣ በዘላቂ ልማትና በውበቷ በምሳሌነት የምትጠቀስ እና ለብዙዎች የመነጋገሪያ ርዕስ ሆና እንደምትገኝ ገልጸዋል።
ከተማዋ ለነዋሪዎች ምቹ፣ የስራ እድል የሚፈጠርባት፣ ለቱሪስቶች ሳቢ እና ትላልቅ የኮንፍረንስ ማዕከል እየሆነች መምጣቷንም ከንቲባዋ አንስተዋል።
ይህም በከተማዋ ትልቅ የስራ እድል እየፈጠረ እና ገቢም እያስገኘ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት እንግዶች ሲመጡ ገመናችንን ለመደበቅ ሲባል ቆሻሻ በብዛት ይከማችባቸው የነበሩ ቦታዎችን በባነርና በቆርቆሮ እስከመሸፈን እንደርስ ነበር ያሉት ከንቲበ አዳነች አቤቤ፣ ዛሬ ላይ ግን የትኛውን ቦታ አሳይተን የቱን እንደምንተው ለመምረጥ ተቸግረናል ብለዋል፡፡
ሁሉም በሚያስብል ደረጃ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የሚማሩባቸው፣ የሚጎበኙ፣ የሚታዩ እና ተሞክሮ የሚወሰድባቸው ቦታዎች ሆነዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎችም ለከተማዋ የሰላም ዘብ በመሆን በመዲናዋ ውስጥ ከፍተኛ የሰላም ለውጥ አስመዝግበዋል ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
በተደራጀ መንገድ በሰላም ሰራዊት ከሚሰሩት በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ነዋሪ እንግዳን በመቀበልና በማስተናገድ ረገድም አዳዲስ ባህሎችንና ልምዶችን እያዳበረ መምጣቱንም ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡
የፀጥታ ኃይሉ፣ የፖለቲካ አመራሩ እና ህዝቡ በቅንጅት በመስራታቸው በከተማዋ ዘላቂ ሰላም መፈጠሩን እና ይህ ድባብ የልማት ስራዎችን እጅግ ፈጣንና ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻሉን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስረድተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች የአዲስ አበባ ከተማን ውብ እና አዲስ ገፅታ እንድትላበስ ላደረጉ ተቋማት፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፀጥታና ሌሎችም ተባባሪ አካላት፣ ለመዲናዋ አመራሮች እንዲሁም ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ታላቅና ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአስማረ መኮንን