ልጆች፡- ስለ “የልጆች ዓለም” ፓርክ ምን ያህል ታውቃላችሁ?

You are currently viewing ልጆች፡- ስለ “የልጆች ዓለም” ፓርክ ምን ያህል ታውቃላችሁ?

ልጆች፤ አዲስ አበባ በኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማት በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ በመሠራት ላይም ይገኛሉ። ከእነዚህ ሥራዎች መካከል የመዝናኛ ስፍራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ልጆች፤ ልማቱ እንደሌሎቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ እናንተንም ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን እናንተ በአንደበታችሁ የመሰከራችሁት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ እናንተ እንድትዝናኑ፣ አእምሮአችሁ ዘና እንዲል ዕድል ፈጥሮላችኋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለእናንተ ለልጆች ትኩረት መስጠቱን አጠናክሮ በመቀጠል አሁን ላይ “የልጆች ዓለም” በሚል መዝናኛ ቦታ እየሠራላችሁ ነው፡፡

ልጆች፤ የልጆች ዓለም ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ በውስጡ ምን ምን መዝናኛዎች እንዳሉትና ምን ዓይነት ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ኃላፊ ጠይቀናል፡፡ እሳቸውም ስማቸውንና ኃላፊነታቸውን በማስተዋወቅ ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ይሰጧችኋል፡፡

“ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ፀሐይ ጌታሁን እባላለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የልጆች ዓለም ፓርክ ግንባታ አስተባባሪ ነኝ፡፡

ልጆች፤ የልጆች ዓለም ማለት እናንተ የምትደሰቱበት፣ የምትዝናኑበት እንዲሁም የምትማሩበት፣ የፈጠራ ሥራዎችን የምታዳብሩበት ቦታ ነው። ይህ ማለት ስብዕናችሁ ወይም ሥነ ምግባራችሁ የሚገነባበት ማለት ነው፡፡”

እየተገነባላችሁ ያለው የልጆች ዓለም ፓርክ የሚገኘው ካዛንችስ ነው፡፡ ፓርኩ በጣም ሰፊ እና በከተማችንም የመጀመሪያው ነው፡፡ በጣም የሚያምር ሆኖ በውስጡ የተለያዩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ ሰፋፊና ጠመዝማዛ የመሮጫ መንገዶች፣ መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ እና የብስክሌት መንጃዎችን ይዟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በባቡርና በትንንሽ መኪናዎች መንሸራሸሪያ ቦታ፣ በዛፍ መልክ የተሠሩ የተለያዩ ውበት ያላቸው መብራቶች፣ የንባብ ባህላችሁን የምታዳብሩበት ቤተ መጻሕፍት፣ የፈጠራና የኪነ ጥበብ ሥራዎች፣ ለሕፃናት ተስማሚ የሆኑ ምግቦችና መጠጦችን የያዘ የካፌ አገልግሎት፣ የተለያዩ የእፅዋት ዝርያዎችና የመሬት ገጽታዎች (መልከዓ ምድር)፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ አገራት የሚታዩ የመጫወቻ ዓይነቶችን የያዘም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ እሴትን የጠበቀ ማለትም ባህላዊ ቤቶች፣ የቡና ሥርዓት፣ ሳይንሳዊ ምርምር የምታደርጉበት የፈጠራ ማዕከልም አሉት፡፡

የልጆች ዓለም ፓርክ የሚሰጠው አገልግሎት በቴክኖሎጂ በተደገፈና ዘመናዊ እንዲሆን ተደርጎ ነው እየተሠራ ያለው፡፡

ፓርኩ ተመርቆ መጥታችሁ ስትዝናኑ የተለያዩ ጥቅሞችን ታገኛላችሁ። ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው የአገራችሁን ባህል ታውቃላችሁ፤ ባህሏን ስታውቁ አገራችሁን የበለጠ እንድትወዱ ያደርጋችኋል፡፡ አዳዲስ ነገሮችን በመመራመርና በመሞከር የፈጠራ ችሎታችሁን ታዳብራላችሁ። አእምሮአችሁ ይነቃቃል፤ አካላዊ እንቅስቃሴን ስለምታደርጉም ለጤናችሁ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንድታገኙ ትሆናላችሁ።

ልጆች፤ አዲስ አበባ ከተማ ለእናንተ ምቹ ሆና እየተሠራች ነው፡፡ የተለያዩ መጫወቻ ቦታዎች ተሠርተውላችኋል። ዕድለኞች ናችሁ፡፡ የልጆች ዓለም ፓርክ ግንባታ ሲጠናቀቅ መጥታችሁ እንድትዝናኑ ጋብዣችኋለሁ፡፡ የዚያን ጊዜ እንግዶቻችን እናንተ ናችሁ፡፡ መልካም የትምህርት ጊዜ ይሁንላችሁ፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review