በአዲስ አበባ የሰንበት ገበያዎች ቁጥር ወደ 282 አድጓል – የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ

AMN – ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ በጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ 264 የነበሩትን የሰንበት ገበያዎች ቁጥር ባለፉት ሦስት ወደ 282 ማሳደግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሐቢባ ሲራጅ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት የሥራ አፈፃፀሙን እየገመገመ ይገኛል።

የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሐቢባ ሲራጅ ፣ ቢሮው በሦስቱ ወራት አገልግሎት በመስጠት፣ አቅርቦትን በማሳለጥ እና ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ረገድ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡

በአገልግሎት ዘርፉ የተገልጋዩን እርካታ የሚያሳድጉ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው ፣ በተለይም የሚሰጡ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የተሰራው ስራ ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል።

ከአቅርቦት አንፃር ያለፉት ጊዜያት በርከት ያሉ ህዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት የነበሩበት እንደሆነ ገልፀው፣ ከመደበኛ አቅርቦት ባሻገር ለበዓላቱ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማቅረብ ረገድ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።

ይህን ለማሳለጥ የሚያግዙ የሰንበት ገበያዎችን ቁጥር ማሳደግና ደረጃቸውን የማሻሻል ስራ ተመከናወኑን ነው የጠቀሱት፡፡

የገበያ ማዕከላትን ቁጥር ከማሳደግ አንፃር ሁለት ተጨማሪ የገበያ ማዕከላትን በለሚ እና በየካ ጉራራ ላይ ወደ አገልግሎት ማስገባት እንደተቻለ ተናግረዋል።

በቁጥጥር ዘርፉም ቢሆን ከ200 ሺህ በላይ ንግድ ፍቃድ የያዙ ነጋዴዎች ላይ የበር ለበር ክትትል መከናወኑን አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት የቢሮው አፈፃፀም 96 በመቶ እንደሆነም ወ/ሮ ሐቢባ ሲራጅ አስታውቀዋል።

የንግድ ፍቃድ ዕድሳት፣ መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓቱ ማስገባት እና በር ለበር የሚደረግ ክትትል ላይ መጠነኛ ክፍተቶች መስተዋላቸውን ያነሱት የቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ሐቢባ ፣ በቀጣይ ሦስት ወራት በአፅንኦት ሊሰራባቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በላይሁን ፍስሃ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review