AMN ጥቅምት 5/2019

ከተሞች ሲለወጡ አፍሪካ ወደ ፊት ትራመዳለች ፤ አዲስ አበባም የዚህ ታላቅ ጉዞ መሪ እየሆነች ነው።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች ኢኒሼቲቭ ፎረምን አስተናግዳለች።
በመድረኩም ከተማዋ በትውልድ ግንባታ ላይ በተለይም በቀዳማይ ልጅነት ልማት ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች እና እየተሰሩ ያሉ ተምሳሌታዊ ስራዎች በመስክ ጉብኝት በአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች ልምድ ተወስዶባቸዋል።

አዲስ አበባ የመደመር መንግስትን እሳቤን በሰው ተኮር ልማት ውስጥ በማካተት፣ የዜጎችን ቀጥተኛና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ለውጥ እያመጣች ትገኛለች።
ይህ ለውጥ በራዕይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን፣ በተጨባጭ፥እና በዘላቂ የልማት ውጤቶች እየተገለፀ ነው።
የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች የአመራር ኢኒሼቲቭ (AMALI) ዋነኛ ዓላማ በአህጉሪቱ የሚገኙ ከተሞች የልማት ለውጥ እንዲፋጠን ማድረግ ነው።
አዲስ አበባም በምታከናውነው አስደናቂ የልማት ጉዞ ይህ ራዕይ ወደ ተግባር ሲቀየር ምን ዓይነት ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል በግልጽ እያሳየች ነው።
ከተማዋ የኢኮኖሚ መዋቅርን ለመለወጥ፣ ሁሉንም ያሳተፈ ዕድገት ለማረጋገጥ እና የበለጠ ለማበልጸግ በቁርጠኝነት እየሠራች ነው።
በዚህም ዘመናዊ፣ ለሁሉም ዕድል የሚፈጥርና በባህል የበለጸገ ከተማ ለመሆን ያላትን ጉዞ እያጠናከረች ትገኛለች።
ከአፍሪካ የከተሞች ማዕከል (ACC)፣ ከቢግ ዊን ፊላንትሮፒ (Big Win Philanthropy) እና ከብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ (Bloomberg Philanthropies) ጋር የተመሠረቱ ትብብሮችም የዚህን የለውጥ ጉዞ በተጨባጭ ለመመልከት ዕድል እየፈጠሩ ነው።
በእነዚህ ትብብሮች አማካይነት የከተማዋ የልማት ተነሳሽነቶች በከተማ ኑሮ ላይ የሚያመጡት ለውጥ እየታየ ነው።
እነዚህ ጥረቶች የነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻልና የተሻለ የከተማ ኑሮ ልምድ ለመፍጠር እንዴት እየረዱ እንደሆነ ያሳያሉ።
ይህ ደግሞ ልማት በዕቅድ ወረቀት ላይ ብቻ ሳይቀር በሰዎች ሕይወት ውስጥ መታየት እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው።
የአዲስ አበባ የለውጥ ጉዞ ለመላው አፍሪካ ጠንካራና ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል።
ራዕይ ያለው፣ ብቃትን የተላበሰና ለለውጥ የሚያንቀሳቅስ የፖለቲካ አመራር ሲኖር፣ ከተሞች ያላቸውን እምቅ አቅም ወደ ሚታዩ ውጤቶች መቀየር ይችላሉ።
ይህ ማለት ጠንካራ አመራር ለከተሞች ለውጥ አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን፣ ለውጡ እንዲፋጠንና ለዜጎች የተሻለ የኑሮ ዕድል እንዲፈጠር ወሳኝ ሚና አለው ማለት ነው።
ከተሞች ሲያድጉ ሕዝቦቻቸውም አብረው ያድጋሉ፤ ከተሞች ወደ ፊት ሲራመዱ ሕዝቦቻቸውም ከእነሱ ጋር ወደ ፊት ይጓዛሉ።
የአዲስ አበባ ተሞክሮም ይህንኑ እውነታ በማሳየት፣ የአፍሪካ ከተሞች በጋራ ለመለወጥ ያላቸውን አቅም ያጎላል።
የከተሞች ለውጥ የሕዝቦች ለውጥ ነው፤ የሕዝቦች እድገትም የአፍሪካን የወደፊት ተስፋ የበለጠ ያበራል! – የከንቲባ ጽ/ቤት